ይህንን የምስራች ቃል ያበሰሩ ከምስራቃዊ
ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ከዳዊት ከተማ በቤተልሔም መንደር የነበሩ እረኞች ናቸው፡፡ (ማቴ 2÷2፣ ሉቃ 2÷5) እነዚህ የቤተልሔም
በግ ጠባቂዎች ቀድሞ ያላዩትን በማየታቸው ሰምተው የማያውቁትን ጥዑመ ዜማ በመስማታቸው የደስታ ጸዳል በፊታቸው በራ
፡፡ ልባቸው የመላዕክትን ቋንቋ ለመስማት በሐሴት ተሞልታለችና ዝማሬያቸው አጥናፍ አቋርጦ ተሰማ፣ ከወዲያኛው ሀገር
ወዲህ አስተጋባ የእረኞቹ ቅላጼ እስከ ሄሮድስ ቅጽረ መንግስት ድረስ ዘልቆ በመግባቱ የልደቱ ዜና የጠላትን ወረዳ አስጨነቀ
ሽብርና ትርምስ ግርግርንም ፈጠረ የመምጣቱን ነገር በጽናትና በጉጉት ሲጠብቁ ለነበሩት ግን የደስታ ቀን የሐሴት ዘመን
የተወደደች ዓመት ሆነ፡፡ በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፣ በቤተልሔም የብርሃን አምድ ተተከለ መላዕክት የእረኞችን ፍርሃት አርቀው
ለዝማሬ በአንድ ላይ ቆሙ… ስብሐት ለእግዚአብሔር በአርያም ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብዕ" የተራራቁት ተቀራረቡ የተጣሉት ታረቁ ለዘመናት ተጋርዶ
የነበረው የጸብ ግርግዳም ፈረሰ "እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን አዋሐደ" (ኤፌ 2÷14) (ኢሳ 9÷2)፡፡
ለህሙማን መድኃኒት (ማቴ 9÷12)
ለቁስለኞች ወጌሻ (ሆሴ 6÷1) በሰቆቃ ለሚያለቅሱ እንባ የሚያብስ (ኢሳ 25÷8) ለተጠሙ የማይደርቅ ምንጭ (ዮሐ 4÷14)
ተገኘ፡፡
ትንሽ ሕፃን ነገር ግን እጅግ ታላቅ፣
ተስፋ ለ5500 ዘመን በኃጢዓት ድርቅ ተመቶ፣ በጽድቅ ርሃብ ተቆራምዶ ለነበረው ዓለም ዝናመ ምህረት፣ ፈውስና ፍጹም መድኃኒት
ተወለደ፡፡
መላዕክት በደስታ ያዜማሉ የድል ዝማሬ
ይዘምራሉ በእኩለ ሌሊት በማኅሌት ያሸበሽባሉ በመገረምና በመደነቅ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የሌለው ዘመን ሊቆጠርለት ሕፃን
መሆኑን አይተው… እረኞችም በመላዕክት ልሳን ከልባቸው ጆሮ የተንቆረቆረውን የደስታ ዜማ የድል ዝማሬ ለአንቀላፉት ሁሉ ተናገሩ
ወደ መንደርም ዘልቀው ገቡ ላልሰማው ሊያሰሙ ያዘኑትን ሊያጽናኑ ተስፋ የቆረጡትን ሊያበረቱ የምሥራቹን ቃል አስተጋቡ… "እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች
እነግራችኋለሁና አትፍሩ፣ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና" (ሉቃ
2÷11)
ሁላችን ጽድቅ ልምላሜ አጥተን እንደ
ርኩስ ሰውም ሆነን ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ በሆነበት ሰዓት ማንም ስለወዳጁ መስዋዕትን ሊቀበልለት ባልቻለበት ክፉ ዘመን
የተገኘ መድኃኒት፡፡
አበው በመስዋዕታቸው በአውራ እንስሳ
በጠቦት ደም ማዳን ባልቻሉበት፣ የአባቶች አባት የሕዝብና የአሕዛብ መገኛ አብርሃምም በልጁ በይስሐቅ መስዋዕትነት ሊያርቅ
ያልቻለውን መርገም፣ ነቢያትም በትንቢታቸው "አቤቱ እባክህ አሁን አድን መድኃኒትም አድርግ ሰማያትን
ቀደህ ውረድ፣ ብርሃንህና ጽድቅህን ላክ ብለው ከመጮህ ውጪ (መዝ 42÷4፣ ኢሳ 64÷1) መዝ 143(144) ÷7-8
አጥንታቸውን ቢከሰክሱ ደማቸውን ቢያፈሱም ቅሉ በአዳምና በሔዋን አለመታዘዝ በመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሕግ ማፍረስ ትዕዛዝ መሻር፣
በሰው ልጆች እምነት ማጉደል ምክንያት ከመጣብን መከራ ከተፈረደብን ፍርድ ከተጓዝንበት የሲኦል ወህኒ ግን መታደግ አልቻሉም
ነበር፡፡
ነገር ግን የተቆጠረው ሱባኤ የተነገረው
ትንቢት ሲደርስ ግን እግዚአብሔር እንደገና አየን አንድ ልጁን ላከልን ሰው ሆነን ተፈጥረን ሰው መሆን ቢያቅተን ሰው መሆንን
አስተምሮ ይቤዥን ዘንድ ሰው ያልነበረው ሰው ሆነ ቃል ሥጋን ተዋሐደ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረትም ተገለጠ (ዘፍ 1÷3፣ ዮሐ
1÷14) ራሱ ለራሱ ባዘጋጀው ማህፀን ተወስኖ ማንም ባልሰራው ማንም ባልገባበት ወደፊትም
ማንም ሊገባበት በማይቻለው ከተማ አደረ፣ በምስራቅ በኩል ባለው
በመቅደሱ በር ገባ" (ሕዝ
41÷1፤ ዮሐ 1÷14) ኢሳ 60÷14) ከሕግ በታች ሆኖ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተፀነሰ ጊዜው ሲደርስ ታላቅ አምላክ ስሙም
ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ህፃን ሆኖ ተወለደልን፣ የዘንዶውን ራስ ይቀጠቅጥ ዘንድ ወንድ ልጁ
ተወለደለን፡፡
ብርሃን ወደ ዓለም መጣ ሁሉ በጨለማ ሳሉ
ሳይነጋ ነጋ፣ ሳይጠራ ነጋ፣ ጨለማው ሊገለጥ ብርሃን ሊያሸንፍ ነጋ፣ የተደበቀው እንዲታይ የተሰወረው እንዲገለጥ እንቅፋት ሁሉ
ሊወገድ ኃጢዓት ሁሉ ሊሰረይ በቤተልሔም መንደር በከብቶች ግርግም በእኩለ ሌሊት ነጋ የዘመናት የእንባ ጎርፍ ሊነጥፍ ጨለማውን
ገላልጦ ብርሃን ተገለጠ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ የተባለው መድኃኒት (የዓለም መድኃኒት) ነው፡፡
ይህ ነው መልካሙ ዜና በመላዕክት ልሳን
ተነግሮ በእረኞች የምስራች ቃል ወደ ዓለም ሁሉ የተዳረሰው፡፡ ይህም ሲሆን ሱባኤ ተቆጥሮለት ትንቢት ተነግሮለት እንጂ እንደ
እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የመጣ አይደለም፡፡ "እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው ወደ
ማደሪያው እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን" መዝ 131÷1 "አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አዕላፋት መካከል
ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል" (ሚክ 2÷2) "እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም
አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች" (ኢሳ 7÷14) በማለት ነቢያት እንደተገለጠላቸው መጠን
ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡
ነገር ግን ቅዱሳን አበው ቅዱሳን ነቢያት
ሊያዩት የተመኙትን በትንቢት የተቃኙትን ሳያዩ አለፉ፣ ትንቢቱ ግን ተፈጸመ ንጉሥ ክርስቶስ ተወለደ ለልጅ ልጆቻቸው ታየ፣
የማይታየው ታየ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ የተሰወረው ተገለጠ እወርዳለሁ እወለዳለሁ ያለው ጌታችን እግዚአብሔር መድኃኒታችን ኢየሱስ
በከብቶች ግርግም ተገኝቶ "ወረድኩላችሁ ተወለድኩላችሁ በማለት በግዕዘ ሕፃናት አለቀሰ
በጨርቅ ተጠቀለለ ከዚህ የበለጠ ግሩምና ድንቅ ዜና ታላቅም የምሥራች የት ይገኛል ከወዴትስ ይሰማል፡፡
በእውነትም ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ
ለደቀመዛሙርቱ እንዳለ "የምታዩትን የሚያዩ ብፁዓን ናቸው እላችኋለሁና እናንተ
የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገስታት ሊያዩት ወደዱ አላዩምም የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙም" (ሉቃ 10÷23-24) መንክር ስብሐተ ልደቱ በማለት እኛም
የምስራቹን እናስተጋባ የድል ዝማሬን እንዘምር፡፡
ቃለ ሕይወት ያሠማልን፡፡
ReplyDelete