Monday, December 15, 2014

የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስለ ክርስቶስ ስለ አንዲት ሃይማኖት ያደረጉት መንፈሳዊ ተጋድሎ

 ክፍል ሶስት፡-

ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ!!! ሮሜ 13፡7
አባታችን በሃይቅ ከእየሱስ ኖሃ ጋር እግዚዓብሄርን በማገልገል ለ12 አመት ከቆዩ ቡኋላ በጸሎት ላይ ሳሉ ምንግዜም ከአባታችን ተክለ ሃይማኖት የማይለይ የእግዚዓብሄር መላዕክ ቅዱስ ሚካኤል ከድንገት ከምድር ነጥቆ ወደ ሰማይ አወጣቸው ነብያት እግዚዓብሄርን በከፍተኛ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት ብለው እንደተናገሩ አባታችን በእግዚአብሄር ዙፋን ፊት ቀረቡ አእላፍ መላዕክት ሲያመሰግኑት አዩ ከዚህ ቡኋላ ክፍልህ ከሃያራቱ ካህናት ጋር ይሁን የሚል ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ አባታችንም የወርቅ ጽና ይዘው ከሃያራቱ ካህናት ጋር ሃያ አምስተኛ ሆነው በሰማይ ያጥኑ ጀመር አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ በማይታጠፍ ህያው በሆነ ቃሉ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ እርሱ ከመረጥኩት ጋር ቃል ኪዳኔን ፈጸምኩ እንዳለ አምላካችን እንዲሁ እንደወደከኝ እወድሃለሁ ስምህን ክቡር አደርገዋለሁ በጸሎትህ የሚተመነውን ሰው ሁሉ ስለ አንተ ይድናል መታሰቢያህን የሚያደርግ ሁሉ እኔ በሰማይ አከብረዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ምድር ተመለሱ በዚህ ግዜ ወደ ፊት ስላላቸው ተስፋ ስለ እግዚአብሄር ፍቅር እንደ እሳት ልባቸው ነደደ የእግዚአብሄር መንፈስ ያሉባቸውን መጽሐፍት ያነባሉ ሌትና ቀን እየተጉ ይጸልያሉ እንቅልፍ በአይናቸው አይመጣም ከሰማይ ከተመለሱ በኋላ በሃይቅ ለአስር አመት ኖሩ፡፡

ከሉበት ከሃይቅ ተነስተው ወደ ትግራይ ክልል ዳሞ ወደምትባል ስፍራ አመሩ በዚያም ስፍራ አንድ ተራራ አለ በዚያም ከአባ ዮሐንስ ጋር ተገናኙ በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ለአስራ ሁለት አመት ኖሩ በጾምና በጸሎት አምላካችንን እያገለገሉና እያመሰገኑ ኖሩ ከዚህ ቡኋላ ከድበረ ዳሞ ወጥተው የተራራውን ገደል መውጫና መውረጃ ገመዱን ይዘው መውረድ ሲጀምሩ ሰይጣን ገመዱን በጠሰባቸው በዚህ ግዜ ለአባታችን ለጻዱቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስድስት የጸጋ ክንፎች ተሰጣቸው፡፡ የደብሩ መነኮሳት በአከባቢው ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ እያዩኣቸው በተሰጣቸው ክንፎች ከምድር በሰላም ደረሱ፡፡ ኢሳያስ በትንቢቱ እግዚአብሄርን በመተማመን የሚጠባበቁ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ ይወርዳሉ ብሎ እንደጻፈ፡፡ ከግዜ ቡኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በክንፋቸው ከመሬት ባረፉበት ስፍራ ቤተ-ክርስቲያን ተተከለ፡፡
አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ዋሊ ገዳም ገብተው ከተሰወሩ መነኮሳት ጋር ተገናኝተው የእግዚኣብሄርን ሰላምታ ተለዋወጡ ከዚያም ተነስተው ወደ ሃውዜን ገዳም ሄዱ በገዳሙ ከመነኩሳት በረከትን ተቀብለው አባታችንም ባርከዋቸው ትግራይንና አከባቢዋን እየዙሩ ባረኩ ከዚህ ሁሉ ቡኋላ ወደ እየሩሳሌም አምርተው በዚያ ክርስቶስ እግሮቹ ያረፈበትን ሁሉ እስከ አረገበት ስፍራ ድረስ ሂደው ጎበኙ በዮርዳኖስም ተጠመቁ፡፡
አባ ዮሐንስ አምስተኛ ከግብፅ ሲመጡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጵጵስና ስራቸውን እየሰሩ ነበር አባ ዮሐንስ ለአባታችን መልዕክት ላኩ ምክኒያታቸው በሹመት ይጣሉኛል የሚል ስጋት ስለ ነበረባቸው መጥተህ እንነጋገር ብለው ላኩ ነገር ግን አባታችን ተክለ ሃይማኖት ትህትና በተሞላ ቃል እኔ አንድ ሚስኪን ከጳጳስ ጋር እንደምን እነጋገራለሁ ነገር ግን ትዕዛዝ ነውና ትዕዛዛቸውን አክብሬ እሄዳለሁ አሉ፡፡ አባ ዮሐንስም ከፊል ኢትዮጵያን እኔ ከፊሉን ደሞ አንተ ሁነን እናገልግል ብለው ጥያቄ አቀረቡ አባታችንም እርሶ ከመጡ እኔ ወደ ቀድሞ ስራዬ እመለሳለሁ ብለው ተሰናብተው ተመለሱ፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እድሜያቸው ሰባ አጋማሽ አከባቢ እንደደረሰ ገዳምን ለመመስረት ወደ አሰቦ ወደ ደብረ-ሊባኖስ ወደ አቡነ ሊባኖስ የጥንት ቦታ አመሩ፡፡ ይህን ቦታ አንድ ጠንቋይ ወርሶት ተደላድሎ ተቀምጦ ነበር ያገኙት በዚያ በዋሻው ውስጥ ገብተው እግዚአብሄርን በጠራሁት ጊዜ ከጠላቶቼ እድናለሁ ብሎ ዳዊት በመዝሙሩ የጻፈውን እያነሱ ይጸልያሉ፡፡ የጠንቋዩ ስም ሃራስ ነበር ይህም ሰው በአባታችን ጸሎት ምክኒያት አከባቢውን ለቆ ጠፋ፡፡ አባታችንም ይህን ቦታ ባርከው በ1267 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስን መሰረቷት በዚህ አከባቢ የአባታችንን ታሪክ ዝናቸውን የሚያውቁ ሁሉ ተሰብስበው ነበር ደሞም ከዚህ ቡኋላ አባታችን እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ይወዱ ስለ ነበር በስሟ ተሰይሞ የነበረውን የእግዚኣብሄርን ታቦተ- ጽዮን አስመጥተው ዋሻውን ከፍለው በሰሌን ጋርደው በዚያ አኖሩት፡፡
አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በጸሎታቸው ከዋሻው ውስጥ ውሃን አፈለቁ ይህ ውሃም የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ውሃ ይባላል፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ በውሃ ላይ ነውና የአባታችንም የስም ውኃ እንደ ጸበል ያገለግላል አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዝናን የሰሙ ሁሉ ወደ አባታችን እየቀረቡ የምንኩስናን ቀንበር የሸከማሉ፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በምድረ አሰቦ/በደብረ ሊባኖስ ሃያ ዘጠኝ አመት ኖሩ ሰውነታቸውም ደከም ለእርጅናም ደረሰ እንደ ወትሮው በመንቀሳቀስ የእግዚኣብሄር የሆነችውን ወንጌልን መስበክ ማስተማር ባይችሉም በደብረ ሊባኖስ አንድ ቦታ ቆመው መጸለይና እግዚኣብሄርን ማመስገን ወደዱ፡፡ ቁመው በመጸለይ ሌተ-ቀን እየተጉ ለብዙ ጊዜያት ተጓዙ አብዝተው በመቆማቸው የተነሳ የአንድ እግራቸው አገዳ ወለቀ የአከባቢው መነኩሳት በጨርቅ ጠቅልለው ቀበሯት፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በአንዲት እግራቸው ለሰባት አመት ያህል በአንዲት እግራቸው ቆመው ጸለዩ፡፡
ከዚህ ሁሉ ቡኋላ አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተገልፆ ምድራዊ ጊዜህን ጨረስክ ስለ እኔ ብዙ መከራዎችን ተቀበልክ አንድ ሃይማኖትህን ጠብቀሃል መታሰቢያህን ለሚያረግ በጸሎትህ ለሚታመን መታሰቢያ ይሆንህ ዘንድ ቃል ኪዳኔን ሰጠሁህ አላቸው፡፡ የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እረፍታቸው በደረሰ ጊዜ መነኩሳቱን ሰብስበው ይመክሩ ነበር ‹‹ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግስተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም አለምን በአግባቡ የናቀ ሁሉ እንጂ ለክርስቶስ እራሱን አሳልፎ የሰጠ ሁሉ እንጂ እናንተ አስቀድማችሁ የእግዚኣብሄርን ጽድቅ ፈልጉ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የእግዚኣብሄርን ትዕዛዝ አጥባቃችሁ ጠብቁ›› አንድ ቀን አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለአባታችን አንተና ሶስት መነኩሳት በንዳድ በሽታ ከዚህ አለም በሞት እንደሚያርፉ ነገራቸው፡፡ ወዲያው ሶስቱ በንዳድ በሽታ ህይወታቸው አለፈ አባታችን ለቤተ-ክርስቲያኑ ማስተካከል ያለባቸውን እንዲስተካከል ካደረጉ ቡኋላ ነሐሴ 24 ቀን 1296 ዓ.ም በዘጠና ዘጠኝ አመታቸው ከአስር ወር ከአስር ቀናት ኣባታችን በስጋ አረፉ መነኩሳትም በዋሻው ውስጥ ቀበሯአቸው፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በአረፉ በሃምሳ ሰባተኛው አመት በ1354 ዐ.ም ሶስተኛ ጭጌ ለአቡነ ህዝቂያስ አባታችን በራዕይ ተገልጸው አጽማቸውን ወደ ቤተ-ክርስቲያኑ እንዲያስገቡት ነገሩ፡፡ መነኩሳቱም ዋሻው ውስጥ ገብተው መቃብሩን ከፍተው አጻማቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያኑ አስገቡት፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአንዲት ሃይማኖት ያደረጉት መንፈሳዊ ተጋድሎ የአምላካችንን አምላክነት ሃይሉንና ግርማውን የሚመሰክሩ ቡዙዎችን በአንድ ሃይማኖት እንዲታነጹ በክርስቶስ ክርሲቲያን እንዲባሉ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙዎችን በአንድ በቀደመች ሃይማኖት እንዲኖሩ ያደረጉ ጻድቃን ሰማዕታትን የሚያከብሩ ታላቅ አባት የኢትዮጵያ ብርሃን ሃዋርያ መነኩሴ ነበሩ፡፡
እንግዲህ የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የህይወት ታሪካቸውን በክፍል ከፋፍለን አይተናል የዛሬዎቹ መናፍቃን አይደለም እነዚህን አባት ቀርቶ በአምላካችንና በአምላካቸው ላይ የሚሰነዝሩት የወረደ ቃላት አምላክነቱን ሃያልነቱን ፈራጅነቱን በመጠራጠር እናቱ በሆነችው በድግል ማርያም ላይ የሚያወርዱት ትችትና ነቀፌታ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡
ቅዱሳንን የሚመርጥ እግዚኣብሄር ነው ደሞም የሚኮንን እርሱ ብቻ ነው እርሱም አምላክነቱን ሃያልነቱን ተዓምራቶቹን እርሱ በመረጣቸው ቅዱሳን በኩል ይፈፅማል ለዚህ አላማ የሚመረጡት ቅዱሳን ላይ ፀጋውን አሳድሮ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚኣብሄር በአባታችን በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኩል ያደረገውን ተዓምር እኛ ኦርቶዶክሳውያን እናምናለን መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከህጻንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ እየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጽሐፍቶችን አውቀሃል፡፡ የእግዚኣብሄር ሰው ፍጹምና ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚ/ር መንፈስ ያለበትን መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ለብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል›› 2ኛ ጢሞ 3÷15-16/17
የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከትና ምልጃ አይለየን፡፡ ብቻውን ለሆነውና አለምን ሁሉ ላዳነው አምላክና መድሃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለም ድረስ ለጌታችን ለመዳህኒታችን ለእየሱስ ክረስቶስ ክብርም ስልጣንም ሃይልና ግርማ ለእርሱ ይሁን የእናቱ የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ጸጋዋና ምልጃዋ አይለየን፡፡ አሜን

No comments:

Post a Comment