Friday, January 29, 2016

አስተርእዮ ማርያም (ጊዜ እረፍታ ለማርያም )





    ጥር 21 በዚህች ዕለት ስለሰው ልጅ አንድ ጊዜ አይደለም ሰባት ጊዜ ልሙት ያለች ለፍጥረት ሁሉ የምታዝን ከርህራዬዋ ብዛት የተጠማን ውሻ በወርቅ ጫማዋ ያጠጣች አባቶች ቢወዷት ሶልያና ያሏት ተወዳጅ እናታች...ን ድንግል ማርያም በ 64 ትአመቷ ዐረፈች። ነፍሷ ከስጋዋ የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትና ድንግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት፤ እጁዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው። በዚያን ጊዜ ጌታችን ንፅህይት ነፍሷን ከስጋዋ ለይቶ ወሰደ። እንደሌላው ፍጥረት ሁሉ የድንግልን ሞት ተናግረን ዝም የምንል አይደለም ይልቁንም ሞትን ድል እንዳረገው እንደ ልጇ እርሷም መነሳቷን እንመሰክራለን እንጂ ። "ማርያም ሞተኪ ይመስል ከብካበ" እውነት ነው የድንግል ማርያም ዕረፍት በመልአክት በብዙ ዝማሬ የታጀበ ሥለነበር ደስታ ሠርግ ነው የሚመሥለው። የሕይወት የድህነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በጸሎቷም ከክፉ ነገር ይጠብቀን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

     እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማነው፡፡ እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የወልድስ ማደሪያ የሆነ ማነው፡፡ እንደ እመቤታችን ማርያም የመንፈስ ቅዱስ ቤት የሆነ ማነው፡፡ ለሰው ኃጢአት ሣይሠራ መኖር ይቻለዋልን ከአራቱ ባሕሪያት ከተፈጠረ ሰው ከመቤታችን በቀር እሳትን የተሸከመ ኃጢአትንም ያልሰራ የለም እመቤታችን ማርያም ከመላእክት ይልቅ ንፅሕት ናት እመቤታችን ማርያም ከሴቶች ሁሉ ትበልጣለች፡፡ የመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡ የእመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፡፡ የአምላክን መልክ ይመስላል፡፡ እመቤችን ማርያም ንጽሕት በመሆኑዋ አምላክን እንዲያድርባት አደረገችው፡ እመቤታችን ማርያም ለአምላክ የደስታ ማደሪያ ሆነችው፡፡ እመቤታችን ማርያም አምላክን በድንግልናዋ ወለደችው፡፡ እመቤታችን ማርያም በነቢያት ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በሐዋርያትም ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፍጥረት አንደበት ትመሰገናለች የቤተክርስቲያን ልጆች አክብሯት ለኛ ለኃጥአን መድኃኒታችን ስለሆነች ፡፡ በጎ አገልግሎትም ለሚያገለግሉት ዋጋውን ትሰጠዋለች ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቦናችሁ እመኑባት እሷ መድኃኒታችን ናትና፡፡ በሥዕሏ ፊት ስገዱ ለሥዕሏም ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ ስም አጠራሩምአይታወቅ፡፡ /ተዓምረ ማርያም መግቢያ/

    ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡ ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡ .የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅስስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ባባ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ ቦሃላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡አንድም በዓሉ-፡ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነት ተወልዶና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በተገለጠበት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር የ“አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል፡፡ አስቀድመው አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ ተበትነው ነበርና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሁሉም ደመናን ጠቅሰው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መርቶ አመጣቸው እንጂ ለምን እንደመጡ አያውቁም ነበር፡፡ እመቤታችንም ለምን እንደመጡ ጠየቀቻቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ሆይ! የመምጣታችን ምሥጢርማ እኛ አንቺን እንጠይቅ እንጂ አንቺም እኛን ትጠይቃለሽን? ሁላችንም ለምን እንደመጣን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ እኔ አስቀድሜ በአንጾክያ ነበርኩኝ አሁን ግን እነሆ እዚህ ነኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁኝ ግን አላውቅም” አላት፡፡ እርሷም ሁሉም በአጠገቧ በተሰበሰቡ ጊዜ የሚሆነውን ነገር አስቀድማ ከልጇ ከወዳጇ አውቃ ተዘጋጅታ ነበርና ለምን እንደመጡ (ዕረፍተ ሥጋዋን ለማየት እንደሆነ) ነገረቻቸው፡፡ ሌሊቱንም በሙሉ በጸሎትና በማኅሌት ደግሞም በዝማሬ ሲያመሰግኑ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተወደደችው እናት በረከቷን አሳድራባቸው በሰላም አንቀላፋች፡፡ ነፍሷም በዐብይ ዕልልታና በታላቅ ምስጋና በመላእክት እጅ ወደ አምላኳ ሄደች፡፡ ኋላ ሐዋርያቱ ዮሐንስን ሲያገኙት፡- “እመቤታችን እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ዐርፋለች” አላቸው፡፡ የቀሩት ሐዋርያት “ዮሐንስ ያን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ አይቶ እኛስ ሳናይ እንዴት እንቀራለን?! አቤቱ ለእኛም ቸርነትህን አድርግልን” ብለው በነሐሴ መባቻ በአንድነት ሆነው ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርብ የአንድ ሳምንት ጾምና ጸሎት ጀመሩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ማብቂያ ዕለት ነሐሴ 14 ቀን እሑድ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ መልአኩ ከገነት አምጥቶ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ልመናቸው ስለ ተፈጸመላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት አመስግነው በዚያችው ዕለተ እሑድ ቅዱስ ሥጋዋን ወስደው ቀብረውታል፡፡ እርሷም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ማክሰኞ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ- እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘው ይህ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይታ የመነሣቷ እውነታ ነው፡፡ የአዛኚቱ ድንግል አማለጅነትና በረከት አይለየን፡፡ ሁላችንም ባለንበት ይህ ታላቅ በዓሏን እያሰብን ጸልየን የበረከቷ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment