Tuesday, January 12, 2016

የሰርጎ ገብ መናፍቃን/ሃራ ጥቃ መናፍቃን/ ዋና ዋና መለያ ባሕርያት/ምልክቶች (ክፍል 3)


     


    የሰርጎ ገብ መናፍቃን/ሃራ ጥቃ መናፍቃን/ ዋና ዋና መለያ ባሕርያት/ምልክቶች

    1. ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ስለቅዱሳን መላእክት እንዲሁም ቅዱሳንና ሰማእታት ርእስ አድርገው አያስተምሩም አይሰብኩም።
    2. በስብከቶቻቸው ውስጥ ለ...ምሳሌ ስለ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ስደት ስቅለት ትንሳኤ ወዘተ ሲያስተምሩ ከእርሱ ተለይታ ስለማታውቀው እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ፈጽሞ አያነሱም።
    3. ስለጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲያስተምሩ የጌታን ስሙን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ብዙው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚጠሩት ባለ ይትበሃል አይጠሩትም። በአብዛኛው የሚጠቀሙት በመናፍቃኑ ይትበሃል ብቻ ነው።


    4. ስለ ጌታችን መድኃኒታችን እና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች አምላክነቱን የተናገረባቸውን ከአባቱ ጋር አንድ ነን ያለባቸውን እኔን አያችሁ ማለት እርሱን አያችሁ ማለት ነው ከራሱ ጋር አስታረቀን... ወዘተ የሚሉትን ጥቅሶች ሳይሆን አገላለጻቸው ራሱን ዝቅ ያደረገባቸው የሚመስሉትን ለሰው አርአያነትንና ትሕትናን ያሳየባቸውን ጥቅሶች....ከሙታን ባስነሳው... ከአባቱ ጋር አስታረቀን ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚገባ የለም...ስለምን ተውኸኝ...ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ...በአብ ቀኝ ያለው ስለእኛ የሚማልደው...ጠበቃችን...ወዘተ አይነት ትርጉም የሚፈልጉ አነጋገሮችን ወስደው በሰው ሰውኛ እንደመሰላቸው እየተረጎሙ ማስተማር ነው
    5. በትምህርታቸው ጊዜ ከገድላት ተአምራት ድርሳናት ወዘተ በፍጹም አይጠቅሱም።
    6. ስብከቶቻቸው ሰዎች ከሰሩት ሃጥያት ንሰሃ እንዲገቡና ለቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ እንዲበቁ ማበረታት ሳይሆን ሕዝቡ ፈጣሪውን ምንም የማያውቅ ያላመ እና ያልተጠመቀ ይመስል እንደ አዲስ እንደገና በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን ልክ መናፍቃን የሚሉትን ጌታ መቀበል እንደሚያስፈልግ ይለፍፋሉ።
    7. መዝሙሮቻቸው በአብዛኛው ከዘፈን የተወሰዱ ዜማዎች ሲሆኑ ግጥሞቻቸውም በሥጋዊ ኑሮና ችግር ማግኘትና ማጣት ወዘተ ዙርያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ተዝቆ ከማያልቀውና ወቅትን እና ዘመንን ካገናዘበው ፍጹም ሰማያዊ ከሆነው የቅዱስ ያሬድ ዜማና ግጥም ወይም ያን መሰረት ያደረገ ግጥምና ዜማ በፍጹም አይዘምሩም።
    8. እነዚህ ሰርጎ ገብ መናፍቃን በማኅሌት በሰአታት በቅዳሴና በሌሎች የጸሎት ጊዜያት በቤተክርስቲያን በፍጹም መገኘት አይፈልጉም።
    9. እውቀታቸውን በራሳቸው ማስተዋልና ንባብ ብቻ ላይ እንጂ ከመምህራን ዘንድ ጠጋ ብለው ለመማር ትርጓሜ መጽሐፍትን ለማጥናት እንደ አባቶች የቃሉን ትርጉምና ምስጢር አንድም እያሉ መማርና ማስተማርን በፍጹም አይፈልጉም።
    10. በስብከታቸው ውስጥ ሴራቸውን የነቃባቸውን ክፍል የተመኙትን እንዳይፈጽሙ ያደረጋቸውን ማንኛውንም ሰውም ሆነ ማኅበር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም በተደጋጋሚ ሲያወግዙና ሲረግሙ ይሰማሉ። ንዴትና ቁጭትም ይታይባቸውል። በተጨማሪም ስለራሳቸው ብዙ ጊዜ እያነሱ ያወራሉ። እዚህና እዛ ሳገለግል...የሚሉ አባብሎች በብዛት ይጠቀማሉ።
    11. በፍጹም እመቤታችን እና ቅዱሳን ያማልዱናል የሚል ቃል በአፋቸው አይገባም። ማንነታቸው እንዳይታወቅም እመቤታችንን እና ቅዱሳንን በአደባባይ አያማልዱንም አይሉም።
    የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ከክህደት ሁሉ ይጠብቀን።
    የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን መላእክት የጻድቃን ሰማእታት አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን።
    አሜን። 


No comments:

Post a Comment