Thursday, January 14, 2016

ሐራጥቃ ተሃድሶን ልብ የሰጡ ሦስቱ ጽንፎች


“መቀበል፣መደገፍ እና መከተል! ሐራጥቃ ተሃድሶን ልብ የሰጡ ሦስቱ ጽንፎች” ውድ አንባብያን በዕረፍት አልባ ቀንና እንቅልፋ የለሽ ሌሊት ልንታገለው ስለሚገባው ሐራጥቃ ተሃድሶ(ፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ) በአንክሮ መነጋገሩ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ሐራጥቃ ተሃድሶ ሕልም አይደለም! ቅዠትም አይደለም! እንደ ምድር ወገብ የሃሳብ መሥመርም አይደለም! ምዕናብም አይደለም! ሰዎች አልያም ማኅበራት የፈጠሩት ስምም አይደለም! ይልቁንም በዓይን የሚታይ፣በጆሮ የሚሰማና እና በእጅ የሚዳሰስ የዐደባባይ እውነት እንጂ፡፡ ዛሬ ለዚህ እኩይ አካል እዚህ መድረስ ጉልህ አስተዋጽኦ ስላደረጉና ለሐራጥቃ ተሃድሶ ግብዓት ስለሆኑት ሦስት ነገሮች መጻፍ አስገደደኝ፡፡ እነዚህ ሦስት ኩነቶች መቀበል፣መደገፍ እና መከተል ናቸው፡፡
ጠቃሚነታቸው ለሐራጥቃ ተሃድሷውያን ሲሆን ምንጫቸው ደግሞ የሐራጥቃ ተሃድሶን ጉዳት ካልተረዱ ምእመናን እና በገሃድ ሐራጥቃ ተሃድሶን ከሚደግፉ ግለሰቦች ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ጽንፎች ለፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ አራማጆች የዕለት ቀለብ ሆነው በማገልገል ላይ ስለሚገኙ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚህ ድርጊት ውስጥ የምንገኝ ወገኖች ቅጽበታዊ ንቃት ያስፈልገናል፡፡ ዛሬ ዛሬ ባለማወቅ እና በግዴለሽነት የምናደርጋት እያንዳንዷ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ለነዚህ አጥፊ አካላት ጥቅም ማጋበሻ መሣሪያ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ምክንያቱም ሃይማኖት መሠረታዊ ጉዳይ ነውና! ዝርዝር ሃሳቡ በቅደም ተከተል ምን ይመስላል? 1ኛ) መቀበል፡- ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ ሐራጥቃ ተሃድሷውያን የሚለቋቀቸውን በኑፋቄ የተመረዙ፤ሙዝን በኮሶ ዓይነት ስብከቶች፣መዝሙራትና የሕትመት ውጤቶች ሳይመረምሩ እንደወረዱ የመቀበል ጉዳይ ነው፡፡ መነሻ ሃሳባቸውና መድረሻ ቦታቸው ለየቅል የሆኑ ዝርው ስብከቶች፣መዝሙራትና፣የሕትመት ውጤቶች እንደ አሸን በፈሉበት በዚህ ዘመን ያገኙትን ሁሉ መቀበሉ አዳጋች ነው፡፡ ነገር ግን ማን እንደጻፈው፣ለምን እንደጻፈው፣ለማን እንደጻፈው እና መሰል ጉዳዮችን መመርመሩ ከአንድ ሃይማኖተኛ ሰው የሚጠበቅ ዓቢይ ጉዳይ ሆኖ ሳለ በገሃድ ሚታየው እውነታ ግን ይህ አይደለም፡፡ ለብ ለብ የተደረጉ ዜማዎችና ከረገዳ የተቃኙ ዳንኪራዎች መስማት የዚህ ትውልድ መገለጫ ሆኗል፡፡ ቁጥር ማብዛት ላይ ብቻ ያተኮሩ ያልተቃኙ ስብከቶች በየ አደባባዩ ሲያንጎዳጉዱ ተቻኩሎ መግዛት ከልምድ አልፈው ባሕል ሆነዋል፡፡ ትውልዱ እውነትን ከሐሰት መለየት አቅቶት ስንዴውን ከነ እንክርዳዱ፣ፍሬውን ከነ አረሙ እየለቀመው ይገኛል፡፡ እስኪ አሁን ስልኮቻችን እና የቤታችን ሲዲ መደርደሪያዎች ያጀሏቸውን መዝሙራትና ስብከቶች እናጢናቸው? እውን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ፣በሊቃውንት የተቃኙ ናቸውን? እንግዲህ ሥራው የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ አንዳንዶቻችን የጸረ ተሃድሶ ትግሉን ተቀላቅለን ይሆናል ግን ስልኮቻችን ሐራጥቃ ሆኑብን ስንቶቻችን እንሆን? እኛ ነጻ ለመውጣት እየሞከርን ይሆናል ስልኮቻችን፣ኮምፒውተሮቻችን እና ሲዲ ማጫወቻዎቻችንስ ምን እየሰበኩ ይሆን? እዚህ ጋር አንድ እውነት ላንሳ በቅርቡ በደብራችን ማኅደረ ሥብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሣዊሮስ ሰ/ት/ቤት አዘጋጅነት በተዘጋጀው የጸረ-የሐራጥቃ ተሃድሶ ግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር ላይ እጅግ የማከብራቸው የመንፈስ ወንድሞቼ ፍሬ ማኅበረ ቅዱሳን ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ፣ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና ዲ/ን ታደሰ ወርቁ ጥናታዊ ጽሑፍ እያቀረቡ በሚገኙበት ሰዓት አዳራሹ ውስጥ ከታደሙ የአካባቢው ምእመናን የእጅ ስልኮች ውስጥ ጉባዔውን ሲያውኩ ከነበሩት መዝሙር ተብዬዎች ሁሉም በሚባል ሁኔታ ውዴ፣ናፍቆቴ፣ናርዶሴ ተብለው የተሞዘቁ ለዛ የሌላቸው ደረቅ ጩኸቶች ነበሩ፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ጥናቱን ከማቅረቡ በፊት መነሻ ያደረገው ይህንኑ ታዘበውን ከመናገር ነበር፡፡ እኔ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ምእመናኑ የመጡት ሐራጥቃ ተሃድሶን ለመቃወምና ግንዛቤ ለማግኘት ነው ነገር ግን ስልኮቻቸውና የቤታቸው ሲዲ መደርደሪያ ሐራጥቃ እሆኑባቸው መሆኑን አልተረዱትም! አልያም የተሃድሶን እንቅስቃሴ የተረዱበት መንገድ ትክክል አይደለም ባይ ነኝ አልያም እነዚህ መዝሙራት ከተሃድሶነት እንደማያስቆጥር አምነውበትም ይሆናል፡፡ ሐራጥቃ ተሃድሷውያኑም የተጠቀሙበት አንዱና ዋናው መንገድ ይህ ነው፡፡ ያሻቸውን ኑፋቄ እያከሉ አመሳስለውና አቀራርበው ትውልዱን ሲበክሉት እውነትን መርምሮ ከመቃወም ይልቅ በይሁንታ መቀበል ተለመደና ለብዙ ነፍሳት መጥፋት ምክንያት ሆነ፡፡ ሐዋርያው እንዳለው መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከወዴት እንደሆኑ መርምሩ! ወገን እንንቃ! 2ኛ)መደገፍ፡-(ላልቶ ይነበብ) ይህ ሑለተኛው ጉዳይ ደግሞ ሐራጥቃ ተሃድሷውያን ከስህተታቸው እንዳይማሩና እንዳይመለሱ የልብ ልብ የሚሰጥ ከደጋፊ ግለሰቦች የሚዘገንላቸው ቀለብ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የኑፋቄ ስብከታቸውን፣መዝሙራቸውንና፣የሕትመት ውጤቶቻቸውን ሳይመረምር የተቀበለ ሰው እነዚህን ግለሰቦች መደገፉ አይቀሬ ነው፡፡ በመደገፍ አባዜ የተለከፉ ግለሰቦች በምንም ተዓምር እነዚህ ሐራጥቃውን እንዲነኩባቸውም ሆነ እንዲነቀፉባቸው አይፈልጉም፡፡ አንዳንዶች ይህን የሚያደሩጉት ባለማወቅ ሲሆን አብዛኞቹ ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚፋጠኑ አርዮሳውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ደጋፊ ግለሰቦች ሐራጥቃውያኑን የሚደግፉት ኑፋቄአቸውን በመቀበል ብቻም ሳይሆን በገንዘባቸውም ጭምር ነው፡፡ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ይህን የጸረ ተሃድሶ ትግሉን አዳጋች ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ ሚይዘው ይህ የደጋፊነት መንፈስ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎች ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከመቆም ይልቅ ግለሰቦችን በመደገፍ ውድ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ ተስተውለዋል፡፡ ግለሰቦችን የመደገፉ ሁኔታ ኦርቶክሳዊ ትውፊት ካለመሆኑ ባለፈም ምክንያታዊም አይደለም! በየትኛውም የቤት ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያልተስተዋለ ድርጊት ቢኖር ይህ ግለሰቦችን የመደገፍ ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ ማኅበር እንውጣ! 3ኛ) መከተል፡- ይህ ሦስተኛው ጉዳይ የተሃድሶ መናፍቃን የመጨረሻ ግባቸው ሲሆን እዚህ ደረጃ ለደረሱ ግለሰቦች ደግሞ ወደ እውነታው ለመመለስ አዳጋች የሚባለው ደረጃ ነው፡፡ የተሃድሶ መናፍቃን ዋነኛ ዓላማ ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ሲሆን ኑፋቄአቸውን የተቀበለና መደገፍ የጀመረውን ግለሰብ በስተመጨረሻ የራሳቸው ተከታይ አድርገው ይከትቡታል፡፡ መሠረታቸው አስድሞውንም በመብዛት ላይ እንጂ በመዳን ላይ ባለመመሥረቱ ተከታይ ማግኘት የዕለት ምግባቸው ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ለዓመታት ተግተው በመሥራታቸው ጥቂት የማይባሉ ተከታዮችን አፍርተዋል፣በየዋሉበት የሚውል በያመሹበት የሚያመሽና በሚዝናኑበት ሁሉ የሚዝናና መናኛ ማኅበረሰብም ፈጥረዋል፣ማታ እስከ ስድስት ሰዓት ለጉባዔ ተግቶ ለሌሊት ኪዳን እና ቅዳሴ የሚታክት ማኅበረሰብ ፈጥረዋል፣አርብ እና ረቡዕ የልኳንዳ ደጅ የሚጠና ትውልድ ፈጥረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በመከተል አባዜ የመጣ ክፉ ደዌ ነው የማይድን ደዌ! ሆኖም ማንኛውም ኦርቶክሳዊ መከተል ያለበት ክርስቶስን እና የቅዱሳኑን ሕይወት እንጂ ግለሰቦችን አይደለም! መከተልም ካለብን እንደ ድንግል ማርያም ወደ ተወደደ ልጇ የምታደርሰንን፣በትህትናዋ የምታስተምረንን፣እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ምድር ርስት ከነዓን ሚያደርሰንን፣እንደ ኢያሱና አቡነ አሮን ፀሐይን አቁሞ እምነታችንን የሚያፀናልንን እንጂ መነሻ ከሌላቸው መድረሻቸውም ከማይታወቅ ግለሰቦች ጋር የት ለመድረስ ይሆን? እውር እውርን ሊመራው ይችላልን? "ማጠቃለያ" የዚህ መልዕክት ፍሬ ሃሳብ አንደኛው ጥቆማ መስጠት ሲሆን ዋናው ሃሳብ ደግሞ በዚህ ድርጊት ውስጥ ባለማወቅ የገቡ የዋሃንን መታደግ ነው፡፡ ከላይ በየመልዕክቱ መሐል እንደገለጽኩት ማዳን የሚያስፈልገው ባለማወቅ የገቡትን ነፍሣት በመሆኑ መልዕክቱ የሚመለከተን ሁሉ ዛሬውኑ ከዚህ ድርጊት በመውጣት ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ፡፡ በተለይም ስልኮቻችንን እና ቤቶቻችንን ያጨናነቁ የኑፋቄ መዝሙራት፣ስብከቶችና የሕትመት ውጤቶችን ማስወገድ ለመመለሳችን ማረጋገጫ ስለሚሆኑልን የድርጊት ሠዎች እንሁን፡፡ ይህን ማድረጋችን ከሚያስገኙልን ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ትውፊታቸውን ጠብቀው ሚታተሙ መዝሙራት፣ስብከቶችንና የሕትመት ውጤቶችን እንድንሰማ ዕድል የሚሰጠን ሲሆን ከዚህ ባለፈም በተሃድሶ መናፍቃን ተውጠው የነበሩና በቅርብ እየተበረታቱ የመጡትን ኦርቶዶክሳውያን ሰባክያንና ዘማርያንን ይበልጥ ያበረታታል፡፡(ይቆየን)
 (ቢኒ ዘልደታ ጥር 03/2008 ዓ/ም)

No comments:

Post a Comment