የጽድቅ ሐዋርያ ቅ/ጳውሎስ አንድ
ሃይማኖት አንድ ጥምቀት አለ፣ ከሁሉም በላይ የሚሆን በሁሉ የሚሰራ አንድ ጌታ ደግሞ አለ (ኤፌ 4፡9) እንዲል ንጽሕትና ጽድልት፣
ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችው የቀደመችው ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት ከዓለመ መላዕክት እስከ ገነት፣ ከምድር እስከ ሰማይ
የፍጥረት ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር የሚመለክባት ብቸኛዋ መንገድ ተዋሕዶ ናት፡፡ ነገር ግን የበጎ ሥራ ጠላት ዲያብሎስ የሰው ልጆችን
ወደ ሞት መንገድ ለመውሰድ ዘወትር ስለማያንቀላፋ በእውነተኛዋ ሃይማኖት አንጻር፣ እውነት የመሰሉ ድርጅቶች ፈጥሮ በሽንገላና በጥርጥር
በወሰዳቸው የግብር ልጆቹ በመጠቀም አንደበታቸውን አንደበት አድርጎ በእጃቸውም እየጻፈ በክህደት ንግግርና ጽሑፍ እውነተኛይቱን ሃይማኖትና
የተቀደሰ ሥርዓቷን በማፋለስ የቀናውን እያጣመመ ትውፊትን እያጣጣለ በጠላትነት ከተነሳባት ዘመናት ተቆጠሩ፡፡
ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ተዋሕዶን
ለመቃወም የሚነሳሳው ክፉ ሰዎችን መሣሪያ አድርጎ ነው፡፡ ጥርጥርና ክህደት ቀደሞውንም ቢሆን የራሱ ነው፣ የሐሰት አባት፣ የክህደት
መሠረት እርሱ ነውና፡፡ (ዮሐ 8፡44) ስለዚህም ብዙዎች በፈቃድ ለእግዚአብሔር ከመገዛት ይልቅ ለሐሳዊው ለዲያብሎስ ማደሪያ በመሆን
ከብርሃን ክርስቶስ ይልቅ ጨለማውን መርጠው የግብር ልጆቹ ሆነው ለዲያብሎስ መጠቀሚያ የሆኑ በርካታ ናቸው፡፡
ከነዚህ የዲያብሎስ የግብር ልጆች
መካከል በቤተክርስቲያን ታሪክ ተጽፎ እንደምናነበው አበው ቀደምትና ፍጹማን ሊቃውንት በንጹሕ የተዋሕዶ ትምህርት ላይ እንክርዳድ
ዘርቶ የነበረውን መናፍቅ አርዮስን ለማሳፈር ቀዳሚውን ጉባዔ አድርገው በቃልና በጽሑፍ ትክክለኛውን የቤተክርስቲያን ትምህርት በማስተማር
ዲያብሎስንና የግብር ልጆቹን ተከራክረው ረተዋል፡፡
በ325 ዓ.ም(፫፻፳፭) በአፈ ጉባዔው በቅዱስ
እለእስክንድሮስ መሪነት ብዛታቸው ሦስት መቶ አስራስምንት የሚደርሱ (318)፣ ሰለስቱ ምዕት) ፍጹማን ሊቃውንት ትልቁ ቆስጠንጢኖስ
በጠራው ጉባዔ ወልድ ፍጡር ነው ያለውን አርዮስን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው በማስተማር የወልድን ፈጣሪነት አስረድተዋል
ጉባዔውም ጉባዔ ኒቂያ በመባል ይታወቃል፡፡
ሁለተኛው በ381 ዓ.ም(፫፻፹፩) መንፈስ ቅዱስ
ሕጹም በማለት የተነሳውን መናፍቅ ጰጳስ መቅዶንዮስን ለማሳፈር በቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦጥሪት አፈጉባዔነት መቶ አምሳ ፍጹማን ሊቃውንት
፣ በቀዳማዊ ቴዎዶስዮስ ጠሪነት ተሰብስበው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ ፈጣሪ መሆኑን በቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለቃል አስረድተው
መናፍቁን ረትተውታል፡፡ ጉባዔውም ጉባዔ ቁስጥንጥንያ ይባላል፡፡
ሦስተኛው በ431ዓ.ም(፬፻፴፩) በአፈ ጉባኤው
በቅዱስ ቄርሎስ መሪነት ብዛታቸው ሁለት መቶ የሚደርሱ ፍጹማን ሊቃውንት፣ በሁለተኛው ቴዎዶስዮስ ጠሪነት ባደረጉት ስብሰባ የእመቤታችንን
ወላዲተ አምላክነት የካደውና ክርስቶስን ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ተነስቶ የነበረውን መናፍቅ በማሳፈር ከቅዱሳት መጻሕፍት
ማስረጃ በማቅረብ፣ እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ መሆኗንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን መስክረዋል፡፡
ጉባኤውም ጉባዔ ኤፌሶን በመባል ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ከታሪክ መዛግብቶች እንደምንረዳው
ቅድስት ቤተክርስቲያን ፈተና ተለይቷት እንደማታውቅና ነገር ግን ፈተናውን ሁሉ ድል በማድረግ የዲያብሎስን ሽንገላ በመቋቋም እስከ
እኛ ዘመን ደርሳለች፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለውና ልናስተውለው የሚገባን ነገር ቢኖር ፈተናው እንደ የዘመናቱ መለዋወጡን ነው፡፡ ትላንት
ብዙዎችን የሸነገለውንና ጠልፎ የጣለው ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ዛሬም በአየር ሲዞር ያገኛቸውንና የማረካቸው ተኀድሶአውያን የሉተር
አቀንቃኞች ክህደትን ይዘው የእናት ጡት ነካሽ በመሆን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ ተነስተዋል፡፡ ሐዋርያው በመጠን ኑሩ ንቁም ባለጋራችሁ
ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ (1ጴጥ 8:9) ብሎ የተናገረውን ኃይለቃል ባለማስተዋል ብዙዎችም የዋሆች
ክርስቲያኖች እንደ ጠፍ ከብት በመነዳት የጠላት ሰይጣን መሣሪያ በሆኑ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ተነጥቀው ወደ መናፍቃኑ አዳራሽ
ወደ ሞት መንደር በገፍ ገብተዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሃያ ዓመታት በሃገራችን
በኢትዮጵያ ሆነ በአረብ ሃገራትና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለዚህ ጥፋት ተባባሪ የሆኑ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ራሳቸውን
ደብቀው ከቆዩበት ጎሬ ከነክፉ ግብራቸው ለምዳቸውን እየገፈፉ እየተገለጡ ነው፡፡
በ1990 ዓ.ም እነ አባ ዮናስና ሌሎች
መነኮሳት ነን ባዮች ተደብቀው ሲሰሩ የነበረው ሴራ እንደተጋለጠ ሁሉ የዛሬዎቹም ተኩላዎች ከኢትዮጵያ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ (ዱባይ)
እንዲሁም ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ድረስ በተዋህዶ ካባ መንጋውን ሲያስቱ ከነበረበት ለምዳቸው እየተገለጡ መሆኑ ለቤተክርስቲያን ታላቅ
ድል ነው፡፡
እነዚህ አስመሳይ የበግ ለምድ የለበሱ
መነኮሳትና መምህራን ዲያቆናትና ዘማርያን በቅድሚያ ራሳቸውን ሳይፈትኑ እንደ እውነተኞች መነኮሳትና መምህራን በጾም በጸሎት በዕንባና
በስግደት ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈጣሪ ሳያስገዙ ቆቡንና ቀሚሱን በማጥለቃቸው መስቀሉንም በእጃቸውና በአንገታቸው በማድረጋቸው በቶሎ በዲያብሎስ
ሽንገላ ተታለው ድል ተነስተዋል፡፡
ድል መነሳቱም ሳያንሳቸው ቆብ ማጥለቅ፣
ቀሚስ መልበስና መስቀል መጨበጥ ዘወትር ነገረ መስቀሉን ለመዘከር ከመሆኑም በላይ ራስን በመካድ ከፈቃደ ሥጋ፣ ከፍቃደ ሰይጣንና
፣ ከፈቃደ ዓለም ጋር በመታገል እንደሆነ ባለማስተዋላቸው፣ በሃይማኖት አጋንንትን ድል የማድረጊያ መሣሪያ የሆነውን፣ እነ እንጦንስና
መቃርስን የመሰሉ ቅዱሳን መነኮሳት በሚገባ ያከበሩትን ክቡር መስቀሉንና አሳኬማውን በመዘባበት ቀልዱበት፡፡ እንዲሁም እነቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅና አባታችን ተክለሃይማኖት በእውነትና በቅድስና የቆሙበትን አውደምህረትና ወንጌል መሣለቂያና መቀለጃ ማድረጋቸው የተሸናፊነትና
የሐሳዊው መሲህ መንገድ ጠራጊ መሆን እንደሆነ ልብ ብለው ሊያስተውሉት ይገባል፡፡
ከሁሉም የሚገርመውና ምን ያህል የክፋት
ምንደኛ የመናፍቃን አቀንቃኝ መሆናቸውን የምታውቁት ለ ፳፻ (2000) ዓመታት ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲሰበክባት የነበረችውን (የቆየችውን) ቤተክርስቲያንና
አውደምህረቱን ክርስቶስን እንዳልሰበከች በመወንጀል አሁን ግን አሮጊቷ ሣራ ወለደች ሲሉ ይስተዋላሉ፣ እንዲሁም ወደ ጨለማው ገዥ ወደ
ሰይጣን እየሄዱ ብርሃን በራልን እውነት ተገለጠልን በማለት በድፍረት ይናገራሉ፣ ምን ይሄ ብቻ አስተምሮአቸውና ዝማሬያቸው ፍጹም
ኦርቶዶክሳዊ ለዛ የሌለው ይልቁንም የምንፍቅናን ክፉ ጠረንና ሽታን በመሽተቱ ከተለያየ አቅጣጫ ምክር ቢለገሳቸው በጸጋችን ቀንታችሁ
ነው በማለት ምክርና ተግሣጹን ማጣጣላቸው እነሱ እንዳሉት ርትዕትና ቅድስት የሆነችው ቤተክርስቲያን የወለደቻቸው ሳይሆኑ የዲያብሎስ
ግብር ልጆች የመናፍቃን ቅጥረኛና ምንደኛ የእናት ጡት ነካሽ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡
እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን
ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡ ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ
የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ
ታላቅ ነገር አይደለም ፍጻሜያቸው እንደሥራቸው ይሆናልና፡፡ (2ቆሮ 11፡13-15) ተብሎ ተጽፏልና እናስተውል፣ በእነዚህ ክፉ ሰራተኞች
እንዳንሳሳት ራሳችንን ከቢጽ ሐሳውያን ተንኮል እንጠብቅ፡፡
ይቆየን፡፡
_____________________________+++++++++++_________________________________
ይቆየን፡፡
_____________________________+++++++++++_________________________________
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment