ልዑለ ቃል በመባል የሚታወቀው ነቢዩ ኢሳይያስ የከበረውን ንጉሥ የአዳምን ዘር ሁሉ ናፍቆት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያለ ዘርአ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) የሚወለድበትን ዓመት በትንቢት መነጽር እያየ "ለድሆች የምስራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ፤ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ ፤ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ፤ የተወደደችውን የእግዚአብሔር ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽና ና ዘንድ ልኮኛል።"ኢሳ፷፩ ፣፪ እንዳለ ተላኪ ወልደ እግዚአብሔር በባሕርይ አባቱ ፈቃድ በራሱም በእግዚአብሔር ፈቃድ ታሪክ ለመቀየር ተወልዶ መገለጡን በትንቢት መጽሐፉ ላይ መዝግቦልናል።
የደጉ ሳምራዊ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናስብ ረጅም ዓመት ወደ ኋላ ተጉዘን ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመናት አስቆጥሮ የነበረው የነፍሳት ጩኽትና በቃላት ሊገልጹት የሚያዳግተው የነቢያትን ትንቢት መሠረት አድርገን እንደሆነ ልብ ይሏል።
የሰው ልጅ በአርያ ስላሴ ከሰባቱ ባሕርያት በእግዚአብሔር ገቢረ ዕድ ተፈጥሮ ገነትን ያህል ቦታ ቢሰጠውም ትዕዛዝን ሻረ ሕግ አፈረሰ ከእግዚአብሔርም ተጣላ፣ እርግማንንም ተረግሞ ፣ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ፍርድ ተፈርዶበት ወደ ምድረ ፋይድ ተጣለ።
አባታችን አዳምና የሕያዋን እናት ሔዋን ከተድላ ገነት ከተባረሩ በኋላ የጾምና የጸሎት ሱባኤ ይዘው መስዋዕትን አቀረቡ፣ በንስሐ እንባ ወደ አምላካቸው ጮኹ ድምጻቸውም ሰማያትን አልፎ መንበረ ፀባኦት ደረሰ ፤ እግዚአብሔር የሰውን ዝንባሌና ስሜት ከፈጣሪያቸው ለመታረቅ ያደረጉትን ጥረት ተመልክቶ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጁ ተወልዶ መጥቶ እንደሚታደጋቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው ። ነገር ግን ዘመኑ እስከሚደርስ ይህ የዕዳ በደል ከትውልድ ትውልድ እየተንከባለለ ሁሉን እስረኛና ግዞተኛ አደረገ፣ ሁሉን የጽድቅ ደኅ አደረገ ፤ ይህንን ታሪክ ለመቀየር መጀመሪያው አዳም ደሙን አፍሷል ፣አበው መስዋዕት አቅርበዋል ዳዊት በመዝሙሩ ዘምሮአል ነቢያት በትንቢታቸው አብዝተው ጮኽዋል፦(መዝ፵፪፣ ፭ / መዝ፩፵፫፣፬-፰/ ኢሳ ፷፬፣፩- ፯) ነገር ግን የተሰበረውን መጠገን ፤ የተበላሸውን ማስተካከል አልቻሉም።
ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን ላያደርግ የማይናገር፣ ከተናገረም የማያስቀር እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን አሰበ የነቢያቱን ትንቢትም እውን ያደርግ ዘንድ አንድያ ልጁን ለመስዋዕት አቀረበ ፤ እግዚአብሔር ወልድ ከልዕልና ወደ ትህትና መጣ ከዙፋኑ ወረደ ፣ ከብላቴናዋም ከድንግል ማርያም ሥጋን ነሳ የክብር ባለቤት አማኑኤል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በቦታ ተወስኖ በቤተልሔም ከተማ በበረት ውስጥ በግርግም ተወለደ።
ስሙም ድንቅ መካር ኅያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ የተባለውን የጌታችንን የልደት ነገር ወንጌላዊው ሉቃስ "በዚያም ወራት አለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሳር ትዕዛዝ ወጣች፤ ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይኽ የመጀመሪያ ጽፈት ሆነ ፡ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ ፣ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ፀንሳ ከነበረች ከዕጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ " (ሉቃ ፪፣ ፩ -፭) በማለት መዝግቦታል። ይህ የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደው በንጉሥ አዋጅ ሲሆን በዚህም ዮሴፍ እመቤታችንን ይዞ ወደ ቤተልሔም መሄዱ ጌታ ባወቀ የተደረገ አስደናቂ ምስጢር እንደሆነ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የክርስቶስ አስደናቂ የልደት ምስጢር ድርሳኑ ላይ እንዲህ ይገልጸዋል" የዘጠኙን ወራት ሁሉ ስፍራ በፈጸመ ጊዜ የአዳም አስገኚ የሆነው እርሱ በትክክለኛው ወግ መሠረት ለመወለድ ፈቀደ ፣ እርሱም አምዳን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሊጽፈው በፈለገ ጊዜ ሕዝብ በሕዝብ ቆጠራ መዝገብ ይመዘገብ ዘንድ ትዕዛዝ ወጣ ሉቃ ፪፣፩ ትዕዛዛቱም አንድ ላይ ተጣመሩ አንዱ ከላይ ከከፍታ እና ሌላኛው ከታች ከጥልቁ ምክንያቱም የሁለቱ ሥፍራዎች ነገሥታት ሕዝብ ሊቆጥሩ ነበርና፣ ቄሳር በሰብአዊ ቆጠራ መዝገብ ሰዎችን ይጽፋል (ይመዘግባል) ፤ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የተለየ ንጉሣዊ ቆጠራ ያደርጋል የማሰኑትን እየፈለገ ደቂቀ አዳምን በሕይወት መዝገብ ውስጥ ያትማል (መዝ ፹፯ ፣፮) ምድራዊው ቄሣር ሰዎችን ለራሱ ባለ ዕዳ አድርጎ የሚያስገዛበትን መንገድ ይቀይሳል ፣ የተወለደው ሰማያዊ ንጉሥ ግን ባለዕዳዎቹን ይቤዣቸው ዘንድ ባለዕዳዎችን ይመዘግባል። መልዕክታቸው ግልጽ የሆኑ የሁለቱ ነገሥታት መጻሕፍት (መዛግብት) በአንድ ወቅትና ሁኔታ ተከናወኑ፤ ንጉሡ ቄሳር በምድር ንጉሰ ሰማይ ወምድር ወልድም በሰማይ ስሞችን መዝግበዋልና ያ የሕዝብ ቆጠራ የመጀመሪያው ጉዳይ ነበር፤ አንዳች አዲስ ነገር የሰው ዘር ላይ የተከሰተ ይመስል በተገለጡ ነገሮች ውስጥ ምስጢር የሆኑ ነገሮች ይገለጣሉ ፣በሚታዩ ነገሮች ውስጥም ስውር ነገሮች ይበሰራሉ፤ አእላፍ ሰዎች ወደ ባርነት ይበልጥ እየቀረቡ ባለበት ጊዜ አርነታቸው ዳግም በልዑሉ አምላክ ታተመ እያንዳንዱ ሰው ስሙን በየራሱ አገር ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት ትእዛዝ ተላለፈ(ሉቃ፪ ፣፫) ስለዚህም ለአዳም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ስም በዔደን ውስጥ መዘገበለት፣ አገሩ ገነት ናትና በበረከት ምድር ፣በወገኖች ሁሉ መዲና አምላኩ ስሙን ጻፈለት በቀደምት አገሩ በወገኖቹ መካከል እርሱ ስሙን ጻፈለት እና ይህ ምልክት ከሰማይ በተላከ ጊዜ ይህ በምድር ይጻፍ ዘንድ ቄሳር አዘዘ ፤እያንዳንዱ ሰው ወደ ከተማው እና ወደ የሰፈሩ ወይም መንደሩ ይመለስ ዘንድ የመመለስ ምሳሌ ሲሆን ፤ምክንያቱም የተሰደደው አዳም ወደ ዔደን ገነት ይመለስ ዘንድ ነበርና ፤ትእዛዙ በይሁዳ ምድር ላይ የሚገዛ ስለነበር፤ ሁሉም ሕዝብ በቆጠራው ተመዝግበው ነበርና ተቆጣጣሪዎች ወደ ማርያም እጮኛ ወደ ዮሴፍም መጡ ፤እርሱም ይሄድና በዳዊት ከተማ ስሙን ያስመዘግብ ዘንድ እርሱም የድንግልና ውበት ምላት የሆነችው እርሷን እየመራ መጣ በትዕዛዙ መሠረት ስሙን ይጽፍ ዘንድ ወጣ ፤በዚያ ያበራ ዘንድ ንጉሡ ወደ ነገሥታት ከተማ ወጣ በልደቱ የሰውን ዘር ሁሉ በሕይወት መዝገብ ውስጥ ይጽፈውም ዘንድ ፤ብላቴናይቱ ድንግል በንጹህ ማህፀኗ ውስጥ የነገሥታትን ንጉሥ ተሸከመችው ተጉዛም ከዮሴፍ ጋር ወደ ኤፍራታ ወጣች (ሚክ ፭፣፪ )እነርሱም ወደ ንጉሡ ምድር በደረሱ ጊዜ እርሱ የራሱ የሆነውን አወቀ እናም ይገባና በራሱ ግዛት ይቀመጥ ዘንድ ራሱን አዘጋጀ ።" ብሏል።
ብዙ ታላላቅ ነገሥታት ዓለምን በሥልጣኔና በኃይል ለውጠዋል ፤ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዓለምን ሳይሆን የሰው ልጆችን ለመለወጥ ነው የመጣው። ምክንያቱም የተለወጠውን ዓለም ያልተለወጡ ሰዎች ያበላሹታልና የሰው ልጆች ግን ከተለወጡ ታሪካቸው ከተቀየረ የዓለምንም ገጽታ በበጎ ይለውጣሉና።
መተርጉማነ መጻሕፍት እንዳስተማሩን ክርስቶስ በተወለደበት ዘመን በተወደደችው ዓመት የሰው ልጆች በከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ወድቀው እንደነበር ይናገራሉ፦ ዝሙት ፣ራስ ወዳድነት ፣ግብረ ሰዶማዊነት ፣ዘረኝነት ፣ የጥቂት ሀገሮች አምባገነንነት፣ ተስፋ መቁረጥ ፣
ሃይማኖት የፖለቲካ መሣሪያ መሆን እነዚህ ሁሉ በምድር ላይ ያንዣበቡ ጥቁር ደመናዎች ነበሩ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከልደቱ ሌሊት ጀምሮ ከተናቁት ከእረኞች እስከ ምድራዊ ነገሥታት ከፍተኛ በሆነ የሞራል ህግ የዓለምን መልክ ለወጠው።
በእውነትም የነገሥታት ንጉሥ የክርስቶስ ልደት የዓለምን ታሪክ እንኳ ለሁለት ከፍሎታል በክርስቶስ የማያምነው ዓለም እንኳ ሳይቀር ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ ዘመንን ይቆጥራል። በመሠረቱ ክርስቶስ የዓለምን ታሪክ የከፈለው ዓመተ ፍዳን በዓመተ ምህረት ለውጦ ፣አልጫውን ዓለም አጣፍጦ ፣በጨለማውም ዓለም ብርሃን ሆኖ ተገልጦ ነው ። "የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች " (ሚል፬፣ ፫) ተብሎ እንደተጻፈ በልደቱ በኅጢያት ደርቆ ጽድቅ ልምላሜ ጠፍቶት በጨለማ ለነበረው ዓለም ከምስራቀ ምስራቃት ከድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን ከድርቀት ወደ ልምላሜ ብርሃን አሸጋገረ።
ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ በነቢያት ትንቢት መሠረት ትቢተኞችን በትህትና ያስተምር ዘንድ በበረት ውስጥ በግርግም ባለጸጋ ሲሆን ራሱን ደሃ አድርጎ ተወለደ።(ኤፌ፪፣ ፰) ራሱን ባዶ አድርጎ ከልዕልና ወደ ትህትና ዝቅ ብሎ የባርያውን መልክ ሲመስል ህፃን ሆኖ በበረት ተጥሎ በጨርቅ ሲጠቀለል ንጉሠ ነገሥት ሆኖ አምላከ አማልክት ሆኖ በፈጠረው ፍጥረት በሰው ግብር ሰው ሆኖ መገለጡን እግዚአብሔርነቱን እንደመቀት ግን አልቆጠረውም ።"
ነገር ግን እርሱ በበረት ተጥሎ በሲዖል በደይን የወደቁትን ነፍሳት ከእስራት ፈቶ ነጻ አወጣ፣ እርሱ በዚያች ሌሊት ያለ ጠያቂ ባይተዋር ሆኖ ተወልዶ ባዝነውና ተበታትነው ጠያቂ አጥተው የነበሩ የአዳም ልጆችን ሰብስቦ ወደ በረቱ አስገባ።(፩ጴጥ ፫ ፣፲፰ /ዮሐ ፲፣ ፬)
"በሬ የገዥውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም ሕዝቤ ግን አላስተዋለም ።"( ኢሳ ፩ ፣፫ )ተብሎ እንደ ተጻፈ ። ይህንን የብዙ ዎችን ታሪክ የቀየረ ልደት ዛሬም ትውልዱ አላስተዋለም ። እርሱ በኅጢያት የታሰሩትን ሊፈታ በእኩለ ሌሊት በበረት በተወለደበት የልደት ዕለት ዓለም በግዞት ታስሮ በዳንኪራ ና በጭፈራ፤ በስካርና በዘፈን ያድራል፤ ትውልዱ ዛሬም አላስተዋለም። እርሱ በተወደደችው ዓመት በሞራል ውድቀት የሞደቀችውን ዓለም ፤ በግብረ ሰዶም ፤በስግብግብነት፤ በዘረኝነት የተበላሸውን የሰው ልጆች ታሪክ በልደቱ ለውጦ ሳለ፤ ዛሬ ግን ዓለም ውለታውን ረስቶ ዳግም ከብርሃን ወደ ጨለማ ተመለሰ፤ ከትውልዱ ማን አስተዋለ ? ይህንን ጥበብ ማን መረመረ ትውልዱ ባለማስተዋል በኑፋቄና በክህደት በሽታ አልጋ ላይ ከዋለ በርካታ ምዕተ ዓመታት ተቆጠሩ ። በዚህ ክፉ ዘመን የትንቢት መፈጸሚያ እንዳንሆን እርሱ በቄሳር መዝገብ ተጽፎ እኛን በሕይወት መዝገብ የጻፈንን የነገሥታት ንጉሥ እናስተውል፤ እርሱ ከልዕልና ወደ ትህትና ዝቅ ብሎ በበረት ተጥሎ በግርግምም ወድቆ ክብሩን ለክብራችን ጥሎ ከግዞት ያወጣንን ከእስራት የፈታንን የነገሥታት ንጉሥ የልደቱን ነገር እናስተውል ፣እናድንቅ ።
ሊቁ አትናቴዎስ በመጽሐፈ ቅዳሴ ትርጓሜ ላይ የወልደ እግዚአብሔርን በፍጹም ትህትና ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በግዕዘ ህፃናት ራሱን ለዓለም መግለጡን በእናቱም እቅፍ መቀመጡን አስመልክቶ ሲናገር "መንክርኬ ወዕፁብ ወመድምም ዝንቱ ነገር ምንትኑ እሔሊ ወአነክር ።ሀልዎተከኑ ምስለ አቡከ ወአርምሞ ወበቅድስና ፤ወሚመ ከመ ሕፃን ውስተ ሕፅነ እምከ፤
አምላክ ሰው ፡ሰው አምላክ የሆነበት ይህ ምስጢረ ተዋሕዶ በእውነት እፁብ ድንቅ ነው። ማናቸውን አስቤ ላድንቅ ? በመለኮታዊ ባሕርይ ባለመመርመር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ በመመስገን ከባሕርይ አባትህ ከአብ ጋራ በቅድምና መኖርህን ላድንቅን?ወይስ በአምሳለ ህንፃ ተገልጠህ በግዕዘ ሕፃናት ሆነህ በእናትህ እቅፍ መያዝህን? እያለ የዚህን ጥበብ ነገር ያደንቃል። በመጽሐፍ አባቶችህ ለመረመሩት ነገር ትጋ ይልላና (ኢዮ ፰ ፣፯) እኛም ይህን የሰው ልጆችን ታሪክ የቀየረ ንጉሥ ልደት በማስተዋል ሆነን እንመርምር፣ እናድንቅ።
ስብሐት ለእግዚአብሔር በአርያም ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ ፤ከልደቱ በረከት ያሳትፈን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን።
መምህር ዲ/ን ቸርነት ይግረም
ታኅሣሥ ፳፬ ፳፻፱ ዓ.ም
መምህር ዲ/ን ቸርነት ይግረም
ታኅሣሥ ፳፬ ፳፻፱ ዓ.ም
No comments:
Post a Comment