Thursday, September 25, 2014

ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኃቸው

                            


ከላይ በርእስነት ያነሣነውን ኃይለቃል በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ነቢዩ ዳዊት ተናግሮታል፡፡ አባቶች ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት አስቀድሞ ትንቢት አላቸው ሲሉ ትንቢት ይቀድሞ ለነገር" እንዲሉ፡፡ (መዝ. ፶፱÷፬)

የእግዚአብሔር ወዳጅ፣ መዝሙረኛው ዳዊት በትንቢት መነጽርነት የተረዳው ምስጢር ቢኖር መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተሰቀለበት ክቡር መስቀል የሚያድን፣ ከሰይጣን የሚታደግ፣ ከክርስቲያኖች ጋሻ ሆኖ የተሰጠበ በረከት መሆኑን ነው፡፡ ነቢዩ የመስቀሉን አዳንነት የተገነዘበው በተሰጠው የትንቢት ጸጋ ነው፡፡ በቀራንዮ መሥዋዕት የሆነው ቸሩ አምላክ ክቡር መስቀሉን ሊቀድሰው ስለፈለገ ቅዱስ ሥጋውን ቆረሰበት ክቡር ደሙን አፈሰሰበት፡፡


"ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ" ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኃቸው አለ፡፡ ይህም ፈጣሪያቸውን በቀና ምግባርና ሃይማኖት ለሚከተሉ ምእመናን የሚጠተነፍስ ምልክት የሚሆን የዲያብሎስን ድል መነሣት ሰጣኸቸው፡፡ እንዲሁም ለሚፈሩህ ለሚያመልኩህ ከፀብን አጋንንት ይድኑ ዘንድ የማሸነፊያ ምልክትን ስመ ሥላሴ መጥራትን፣ በመስቀል ምልክት ማማተብን በአጠቃላይ የመዳን ምልክት የሆነውን "የመስቀል አርማ" በሐዲስ ኪዳን፣ በዓመተ ምሕረት እንደሚሰጣቸው ያስተረጉማል፡፡

ነቢዩ እንግዚአብሔርን ለሚፈሩትና ለሚያመልኩት ምልክትን የሰጠበትን ምክንያት ሲገልፅ "…ከመያም ሥጡ እምገጸ ቀለበት ወይድኃኑ ፍቁራኒከ፡፡" ለሚፈሩህ ለሚያመልኩህ ምልክትን የሰጠኃቸው ከቀስትፊት ያመልጡና ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ ነው ብሏል፡፡

ቀስት የተባለው መከራ ነፍስ ነው፡፡ እኛ የዳነው መድኃኔዓለም በመስቀል ተሰቅሎ በከፈለልን ካሳ ነውና፡፡ እንዲሁም ቀስት የተባለው አጋንንት ምእመናንን ከመፈተን ያከሙት፣ የሚሰነዝሩት የተንኮል ፍላፃ ነው፡፡ ይህም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ዘፋኝነት፣ ስካር…. ወዘተ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ዲያብሎስ የሚወረውራቸው ቀስቶች ምእመናን የሚያከሽፉት መስቀል ክርስቶስን አምባ መጠጊያ በማድረግ ነው፡፡ ነገረ መስቀሉን፣ ሕማማተ መስቀሉን በማሰብ ጊዜ ሰይጣንና ክፉ የሥጋ ፈቃድ ይሸነፋሉ፡፡ (ገላ ፮÷፬)

ነገረ መስቀሉን ስናስብ ክርስቲያናዊ ንቃትን እንጎናጸፋለን፡፡ ነገረ መስቀሉን በማሰብ ጊዜ የድል አድራጊነት ጸጋ ይሰጣል፡፡ ክርስቲያናዊ ንቃት ማለት የዲያብሎስን የተንኮል አንሣሥ መረዳት ማለት ነው፡፡ የድል አድራጊነት ጸጋ ማለት በፈቃደ ዓለምና በፈታኙ መንፈስ ላይ በፍጹም እምነትና በፍጹም ትህትና መከራከር ኃይል ማግኘት ማለት ነው፡፡ (ኤፌ ፮ , ፲፩ና ፲፫)

ስለዚህ ነው ቅድስት ዕሌኒ አይሁድ በተንኮል ቀብረውት የነበረውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መስቀል ታገኝ ዘንድ በክርስቲያናዊ ንቃት የተጋቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስያናችን በመጽሐፈ ኪዳን የተነገረውን ትምህርት በመያዝ "ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ በዲበ ዕፀ መስቀል ተሰሃከነ እግዚኦ" የሚል ጸሎት ይዛ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም የተሰቀለበትን መስቀል የድኅነትን ምክንያት ነው ብላ ታምናለች፡፡

በጹኑ ሃይማኖታቸውና በቀና ምግባራቸው ከሚታወቁት የኢትዮጵያዊያን ነገስታት መካከል ዐፄ ዳዊትና ልጃቸው ዘርዓ ያዕቆብ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀሉን ከሰናር ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡ ዘንድ ደክመዋል፡፡ ድካማቸውና ፍቅራቸውን የተመለከተ እግዚአብሔርም ቅዱስ መስቀሉ በኢትዮጵያ እንዲያርፍ ፈቃዱ ሆነ፡፡

በመሆኑም አስቀድሞ ሲፈጥራት ለመስቀሉ ማረፊያ ትሆን ዘንድ በመስቀል ቅርፅ ባላናዳት በግሸን ደብረ ከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ በክብር ላኑሩት፣ በሃይማኖት በንስሐ ግሰግሰው ወደ ደጇ የሚደርሱትን በአናቱ ጸሎት፣ በቅዱስ መስቀሉ ይባረካሉ፡፡ የሚያምኑና የሚጠራጠሩ ግን ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር አያገኙም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፣ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡" እንዳለ (፩ኛ ቆሮ፣ ፩÷፲፰፣ ያዕቆብ ፩÷፯-፰)

እንግዲህ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በጸሎትና በምስጋናዋ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኃይለ መስቀሉ ድኅነ እያለች ትዘምራለች፡፡ በማያምኑት መካከል ይህ ምስጋናና ዝማሬ ሲሰማ ሞንነት ይመስላል፡፡ ለክርስቲያኖች ግን ታላቅ ትርጓሜ አለው፡፡ በዚህም ሰይጣንና ሠራዊቱን ዓረማዊያንንም ድል እናደርጋለን፡፡

መድኃኔዓለም ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ አይሁድና አረማዊያን ምራቃቸውን እየተፉ ተዘባብተውበታል፡፡ በሶስተኛው ቀን ግን ሁሉም ዓመድና ትቢያ ሆነዋል፡፡

ዛሬም ቢሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን ስትፈተን የምትጠፋ የምትመስላቸው ሰዎች ካሉ ተሳስተዋል፡፡ የዮዲትና የግራኝ አሕመድ የሱስንዮስና የደርቡቮች ሴራ፣ ቅኝ ገዢዎች የሆኑ የጣሊያን ፋሽስቶች ወረራ፣ ክህደትን ይዘው የነበሩ የማኒ ልጆች ዓላማ፣ የተሐድሶ ከሃዲያን ሴራ እንኳን ሊጥላት ቀርቶ አላንገዳገዳትም፡፡ ዛሬ ብርሃኗ የፈዘዘ የሚመስለው የተዋህዶ እምነት የፍግ እሳት ናት፡፡

በሃይማኖት በፍቅር የጸኑ የተዋሕዶን ብርሃን ያያሉ፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንት የነበረ፣ ዛሬም ወደፊትም የሚኖር መላእክትን የሚታዩና የማይታዩ ዓለማትን እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙትን የሰው ልጆች የፈጠረ ዘላለማዊ አምላክ ነውና፡፡ ከድኅነታችን ምልክት አድርጎ በሰጠን በኃይለ መስቀሉ ተጠብቀን የጽድቁን ወራሽ የምስጋናው ተካፋይ እንዲያደርገን የድንግል እናቱ አይለየን፡፡ (ሚል ፫÷፮፣ ዕብ ፲፫÷፰)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

No comments:

Post a Comment