Wednesday, September 10, 2014

‹‹አዲስ ልብንና አዲስ መንፈስን ለእናንተ አድርጉ›› (ሕዝ 18፡31)



መልካም አዲስ ዓመት

ኃይለ ቃሉን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሚመክርበት ዘመን ከአበይት ነቢያት አንዱ በሆነው በነቢዩ በሕዝቅኤል በኩል ስለብዙ ነገር ተናግሮታል፡፡ ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ ይነገር እንጂ ፍጻሜው ግን እኛም እንማርበት ዘንድ ተመዝግቦልናል፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዋና መልዕክትና መሠረታዊ ዓላማ በምድራዊው የኮንትራት ኑሯችን በዘመን ተሰፍሮና ተወስኖ በተሰጠን ዕድሜ በተለይም በቀሪ ጊዜያችን አሮጌውንና የዛገውን ልብ አውጥተን አዲስ ልብን ገንዘብ እንድናደርግና በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ማሳሳብ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ መጪውን ዓመት አዲስ ብለን እንቀበላለን፡፡ ያላስተዋልነው ግን ዘመን እኛን እያስረጀ ሁል ጊዜ አዲስ እየተባለ መስተናገዱን ነው፡፡ ዘመንን ካነሳን ዘንዳ ስለ ዘመን ጥቂት እንበልና ወደ ተነሳንበት መልዕክት እንመለሳለን፡፡
የዘመናትና የጊዜያት ባለቤት ጊዜን ለሰው ልጆች የሰጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም አለ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ አለ፣ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት የሚያፈራርቅ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰኮንዶች ወደ ደቂቃዎች፣ ደቂቃዎች ወደ ሰዓታት፣ ሰዓታት ወደ ዕለታት፣ ዕለታት ወደ ሳምንታት ሳምንታት ወደ ወራት ወራት ደግሞ ወደ ዓመታት እየተፈራረቁ እግዚአብሔር በቸርነቱ እኛን ያኖረናል፡፡ ትልቁን ብርሃን ፀሐይን በቀን ያሰለጠነ ትናንሾቹንም ብርሃናት ጨረቃና ከዋክብትን በሌሊት ያሰለጠናቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ እነሱም እየተፈራሩቁ ዘመንን ዘመን ያሰኙታል፡፡
የሰው ዘመን ግን በምድር ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በምድር ላይ እንኖራለን፡፡ ‹‹ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ የተወሰኑም ዘመኖችና ለሚኖሩበትም ሥፍራ ዳርቻ መደበላቸው›› (ሐዋ 17፡26) በመሆኑም ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ዓመታትን እንቆጥራለን ዓመታትም በጨመሩ ቁጥር ደግሞ የኛ የሰው ልጆች ዕድሜ ይቀንሳል ምክንያቱም ከተወሰነልን ዘመን ከተሰጠን ዕድሜ ከተፈቀደልን ጊዜ ላይ እየኖርን በመሆኑ ነው፡፡
እግዚአብሔር ግን ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ ነበረ በዚህ ጊዜ ደግሞ አይኖርም አይባልም፡፡ ከዘላለም እስከ ዘላለም እርሱ ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር በባሕርይ ክብሩ ነበረ፣ ዓለምንም ፈጥሮ እየገዛ ያለው አምላክ ነው፣ ዓለምንም ደግሞ አሳልፎ ለዘላለም የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ይህንን ሲያጸና ልበ አምላክ የተባለ ዳዊት ‹‹የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጅህ ሥራዎች ናቸው፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደመጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ትለውጣቸዋለህ ይለወጡማል፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመቶችህ ከቶ አያልቁም›› (መዝ 101፡23) ብሏል በመሆኑም የሚመጣውና የሚሄደው ትውልድ እንጂ ዘመን የጊዜ ዑደቱን ጠብቆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይፈራረቃል፡፡ እግዚአብሔርም የጊዜ ባለቤት እሱ ስለሆነ ወሰን ገደብ ለዓመቶቹም ልክና መጠን የለውም፡፡ ከዘላለም እስከዘላለም የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ሰማይና ምድርም ያልፋሉ ፍጥረታትም ያረጃሉ እርሱ ግን ያው እርሱ ነው፡፡
የሰው ልጆችም በምድር ላይ የምንኖረው ለተወሰነ ዘመን ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ተጠርተን እንሄዳለን በሞት እንወሰዳለን ዘመናትን በየጊዜው እንደወደደ የሚለውጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ ‹‹ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል ጥበብና ኀይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ ;ነገስታትን ያሳልሳል ነገስታትንም ያስነሣል ጥበብን ለጠቢባን ዕውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል›› (ዳን 2፡21) ጊዜያትንና ዘመናትን የሚለውጥ፣ ሌሊቱን ወስዶ ቀኑን የሚያመጣ፣ ክረምቱን ወስዶ በበጋ የሚተካው እግዚአብሔር ነው ይህ የሰው ልጆች የአዕምሮ ጭማቂ ውጤት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ነው እንጂ እኛም እግዚአብሔር እንደረዳን መጠን የምንኖረው በዚህ ውስጥ ነው፡፡
‹‹ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው አንተ ፀሐዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሰራህ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ›› (መዝ 73፡16) እንዲል ቅዱስ ዳዊት ሁሉ የእርሱ ነው ሁሉን ያዘጋጀ እግዚአብሔር ነው፡፡
ከዘመንም ወደ ዘመን የምንሸጋገረው በእግዚአብሔር ፈቃድና ቸርነት ነው፡፡ ጊዜ የሚጨመርልን ዘመን የሚሰጠንም በዘመናችን ንስሐ እንድንገባ በተጨመረልን ዕድሜ ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ነው፡፡
ዓመትን እንደ አክሊል በራሳችን ላይ የሚያቀዳጀን እንደ ዘውድ የሚደፋልን ለዚህ ሰዓትና ለዚህ ዕለት ያደረሰን የእግዚአብሔር ቸርነት ነው፡፡ ማንም ሰው ስላለው ነገር እዚህ ዕለትና ለእዚህ ሰዓት አልደረሰም፡፡ ባለጠጎች ስለገንዘባችን ባለዕውቀቶች ስለዕውቀታችን ባለሥልጣኖች ስለሥልጣናችን ባለጉልበቶችም ስለጉልበታችን ባለዝናዎችም ስለዝናችን ለዚህ ዕለትና ሰዓት አልደረስንም፡፡



 


‹‹በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ›› (መዝ 64፡11) ተብሎ እንደተጻፈ ይህንን የእግዚአብሔርን ምህረትና ቸርነት የምናስብ ስንቶቻችን ነን፡፡ ሰው ደግሞ ጊዜ ካልተሰጠው ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር እንድንኖር ካልፈቀደልን ጊዜ ካልሰጠን ምንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ ወጥተን የምንገባው ተቀምጠን የምንነሣው ተምረን ለውጤት የምንበቃው ሠርተን የምናገኘው ነግደን የምናተርፈው ወልደን የምንስመው እግዚአብሔር ጊዜ ሲሰጠን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ግን የእግዚአብሔርን ቸርነት ረስተዋል፡፡ ጊዜ ዋጋ የሚከፈልበት ቢሆን ኖሮ ዋጋውን ማን ይችለው ነበር፣ ግን እግዚአብሔር ጊዜን የሰጠን ያለዋጋ በነፃ ነው፣ ለምንኖርበት ዕድሜ የጠየቀን ዋጋ የለም፡፡
ታዲያ ጊዜ የሰጠን እግዚአብሔር ደግሞ ጊዜ እንድንሰጠው ይፈልጋል፣ ጊዜ የምንሰጠው ደግሞ ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዲኖሩ፣ እንዲወጡና እንዲወርዱ ጊዜና ሁኔታውን እግዚአብሔር ሰጥቷቸው ሳለ ጊዜ ለሰጣቸው ለእግዚአብሔር ግን ጊዜ መስጠት ተስኗቸው ይስተዋላሉ፡፡ ስለ ዘመን ይህን ያህል ካልን ዘንዳ ወደ ርዕሳችን ዓቢይና ቁልፍ መልዕክት ስንመለስ አዲስ ልብንና አዲስ መንፈስን ለእኛ የምናደርገው ጊዜ ለሰጠን ለእግዚአብሔር ጊዜ በመስጠት ይሆናል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት›› ተብሎ እንደተጻፈ (ራዕ 2፡21)
እግዚአብሔር ጊዜ የሚሰጠው ዕድሜን የሚጨምረው ዓመፃችን ሳይመለከት በደላችን ሳያይ ቀርቶ ሳይሆን ንስሐ እንድንገባ እንድንመለስ እንድንድን ወዶ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልም በእግዚአብሔር መንፈስ በመሆን በክፋትና በተንኮል ለዛገው ለደነደነው ልባችን በኀጢዓትም ላረጀውና ለተበላሸው መንፈሳችና ለውጥ እንደሚያስፈልገው በማሳሰብ አዲስ ልብንና አዲስ መንፈስን ለእናንተ አድርጉ አለ፡፡
ለምን ብንል? ልባችን አርጅቷልና መንፈሳችን ተበላሽቷልና አሁን መታደስ አለብን የልቡና ለውጥ የመንፈስ መታደስ ያስፈልገናል፡፡
ምናልባት አንዳንዶቻችን በዕድሜ አላረጀን ይሆናል ገና ወጣቶች፣ ጎልማሶች አይደለንም ወይ እንል ይሆናል እንዲሁም ገና ብዙ እንኖራለን ብዙ ዕቅዶች አሉን ይሆናል፣ ትዳር ለመመስረት ፣ ዘር ለመተካት ዓይናችንን በዓይናችን ለማየት፣ ሰርተን ለመበልጸግ ፣ ነግደን ለማትረፍ ተምረን ለመመረቅ ወዘተ…
ሌሎቻችንም እኛ መች አረጀን አይናችን አልፈዘዘ ሰውነታችን አልደነዘዘ ሥጋዊ ጤንነታችን አልታወከ ጌልበታችን አልደከመ ሮጠን እንቀድማለን ታግለን እንጥላለን፣ ተናግረን እናሳምናለን፣ ጨብጠን እናቆማለን እንል ይሆናል፣ ነቢዩን የዕድሜ ጉዳይ አይደለም ይህንን ያናገረው ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜ ማን ይሆን ያላረጀው ኀጢዓት ያላስረጀው ሰው ማን ይሆን? መመርመር ያለብን ልባችንን ነው፣ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ነው፡፡
ነቢዩ ሕዝቅኤል ይህንን ቃል ለእስራኤል ዘሥጋ የተናገረበት ምክንያት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን እየበደሉ በብዙ ኀጢዓት አርጅተው ስለነበር ነው፡፡ ‹‹የእስራኤል ቤት ሆይ ስለዚህ እንደመንገዱ በየሰው ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አልፈቅድምና ተመልሳችሁ በሕይወት ኑሩ ኀጢዓትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ንስሐ ግቡ›› (ሕዝ 18፡30) ንስሐ ግቡ ማለቱ ተመለሱ ተጸጸቱ ማለቱ ነው፡፡
ንስሐ ማለት መመለስ ነው መፀፀጽ ነው ያለፈውን ኀጢዓትና በደል መተው ነው ሸክምን ማራገፍ ነው፡፡ ከውድቀት መነሣት፣ ከርኩሰት መቀደስ፣ ለወደፊቱም ከክፋት መራቅ፣ መከልከልና መታቀብ፣ ከኀጢዓትም መጠበቅ ነው፡፡
ኀጢዓት እንቅፋት ነው ያሰናክላል ያዋርዳል ያሳድዳል ራሳችንን እንድንጠላና እንድንጸየፍ ያደርጋል፣ መፈጠራችንን እንድንጠላ ያደርጋል፣ ያውካል ያስጨንቃል ሠላም ይነሣልና፣
እኛንም በተሰጠን ጊዜ በተጨመረልን ዕድሜ ንስሐ ግቡ ተመለሱ አዲስ ልብንና አዲስ መንፈስን አደርጉ ነው የሚለው አንባቢያን ልብ እንበል ‹‹የተጨመረልን ዕድሜ የንስሐ ነው በኀጢዓት የምንረክስበት እግዚአብሔርን የምናሳዝንበት አይደለም ነገር ግን ንስሐ የምንገባበት ነው፡፡ ‹‹ከኀጢዓታችሁ ሁሉ ተመለሱ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ›› ኀጢዓት ሸክም ዕዳ ነውና፡፡ እግዚአብሔር በቸርነቱ ያቁመን እንጂ አንዳንዶቻችን ሸክም ከብዶን እየተንገዳገድን ነው፣ ብዙዎቻችንም በበደላችን ተፍገምግመን ወድቀናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ከቤርሳቤህ ደርሶ በዝሙት በረከሰ ጊዜ ኦርዮንን አስገድሎ እጆቹ በንጹሕ ደም በታጠበ ጊዜ እንደዚህ እያለ ነው ወደ እግዚአብሔር ያለቀሰው ‹‹ኀጢዓቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሏልና እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዷልና›› (መዝ 37፡4)
አታመንዝር የተባለውን ሕግ ተላልፎ ስላመነዘረ አትግደል የተባለውን ሕግ ተላልፎ ንጹሁን ሰው ኦርዮንን በግፍ ስላስገደለ ነው››
ዛሬስ ማነው ያልበደለ? ማን ነው ኀጢዓት ያልሰራ የእግዚአብሔርን ሕግ ያልተላለፈ ሰው ማነው? በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ነኝ የሚል ሰው ይገኝ ይሆን? በባሕርይው ንጹሕ ጻድቀ ባሕርይ ኀጢዓት ለባሕርይው የማይስማማው እንከን የማይወጣለት ነውር ነቀፋ የማይገኝበት አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡
ሌላው ከፍጥረታት በጸጋ ንጹሕት ቅድስት ብፅዕት ነውር የሌለባት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት፡፡
(መኀ 4፡7) ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም›› ተብሎ ተጽፎላታልና፡፡ ሌሎቻችን የበደሉ ዓይነትና መጠን ይለያይ እንጂ ወይ በሥራ ወይ በኀሣብ፣ ወይ ደግሞ በቃል በደለኞች ነን ከአንዱ ብንነፃ ከሌላው አንነፃም፡፡ በመሆኑም የበደላችሁትን በደል ከእናንተ ጣሉ ሸክምን አራግፉ ማለት ዕረፍትና ሠላም ያሳጣንን ይህንን ሸክም መጣል ማለት ነው፡፡ ‹‹ልቤን አነፃሁ ከኀጢዓትም ጠራሁ የሚል ማነው›› (ምሳ 20፡9) እንዲል ጥበበኛው ኀጢዓት አልሰራሁም አልበደልኩም የሚል ካለ እርሱ ይዋሻል፡፡ ምናልባት እኛ በደል ሲባል ኀጢዓት ሲባል የምናነሣው የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያልፈቀደልንን ክፉውን ነገር አልታዘዝንምና እግዚአብሔር የፈቀደልንን የሚጠቅመንን በጎውን ነገር መልካሙን ነገር ካላደረግን ደግሞ ኀጢዓተኞች ነን አልታዘዝንምና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ኀጢዓት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም›› (ዮሐ 1፡8) በማለት ያጸናዋል፡፡ በመሆኑም ጨለማን ተገን አድርገን ደጃፍ ዘግተን ሰው አየን አላየን ብለን የሰራነው ኀጢዓት ብዙ ነውና፣ የበደልነውም በደል አለና አሁን እሱን መጣል አለብን፡፡
ይቀጥላል፡፡    

No comments:

Post a Comment