Saturday, June 28, 2014

‹‹የገሀነም ደጆች አይችሏትም›› (ማቴ16፡18)




ይህንን ኀይለ ቃል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳሪያ ለሊቀ ሐዋርያት ለቅዱስ ጴጥሮስ ተናግሮታል፡፡ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወለድ በተለየ አካሉ ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ፡፡ (ዮሐ 1፡14)
ከንጽሕተ ንጹሐን ከድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ ከዘመን አስቀድሞ የነበረ እርሱ ትንሽ ህፃን ሆኗልና፣ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን በዘላለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ ኀጢዓትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት ይህን ወድዷልና፡፡ ክብሩ ተለይቶት የነበረ ሥጋን ክቡር አምላክ ሊያደርገው የጸጋ ገዥነትን አጥቶ የነበረ ሥጋንም የባሕርይ ገዥ ሊያደርገው ወደደ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ያለውንም ሰው በመሆን ሊገልጠው ወደደ››
(ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 220)




እንዲል ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መድኀኔዓለም ሰው ሆኖ የሰውን ሥጋ ለብሶ ቢመጣ ሰዎች ተሰናከሉበት፣ ክብሩን ትቶ የተዋረደውን አዳምን ሊያከብር ቢመጣ ሰዎች አዋረዱት፣ ሙታንን ሊያስነሳ እውራንን ሊያበራ ለምፃምን ቢያነፃ አጋንንትንና የአጋንንትን ማሰሪያ ቢበጣጥስ በአጋንንት አለቃ አጋንንት የሚያመጣ ብለው በምድራውያን ጠንቋዮች ግብር ሰድበው ለሰዳቢ ሰጡት በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና የመወለዱን ምሥጢር ቢረቅባቸው የዮሴፍ ልጅ ፍጡር ብለው የሁሉን ፈጣሪ አሙት አምላክ ወልደ አምላክነቱን ተጠራጥረው ተሰናከሉበት፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር ጌታችን መስክር ይሆኑት ዘንድ ከዓለም የለያቸውን አስራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ይዞ ወደ ፊሊጶስ ቂሳሪያ ሀገር በደረሰ ጊዜ በአንድ ላይ ጠራቸውና ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅን ማን እንደሆነ ይሉታል?›› ሲል በመንደር ሲወራ የነበረው ሐሜት ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ለማረጋገጥ ጠየቃቸው፡፡ ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ አዳምና ልጆቹን መስላልና ራሱን ‹‹የሰው ልጅ›› ብሎ ይጠራል፡፡ (ዘፍ 3፡22)
ደቀመዛሙርቱም የሰሙትን እንዲ መሰከሩ ‹‹አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርሚያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት›› ማቴ 16፡14
ጌታችንም ወደ ደቀመዛሙርቱ በፍቅር ዘወር ብሎ እናንተስ ከክፉው ዓለም የለየሁአችሁ የእጄን ተአምራት ያያችሁ የቃሌን ትምህርት የሰማችሁ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ አላቸው፡፡ ስምኦን ጴጥሮስም መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ አለው ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ‹‹የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፅዕ ነህ እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያን እሰራለሁ፣ የገሀነም ደጆችም አይችሏትም›› (ማቴ 16፡13-18)
ጴጥሮስ ማለት ቃሉ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ዓለት ማለት ነው፡፡ ጌታ ዓለት ያለው እንደ ዓለት የማይናወጽ ምስክርነት ስለሰጠ፣ የማይለወጥ የማይፈርስ ጽኑ ቃል ስለተናገረ ነው፡፡ ከባሕርይ አባትህ ከአብ ከባሕርይ ሕይወትህ ከመንፈስ ቅዱስ በስልጣን በአገዛዝ በመለኮት በህልውና የተስተካከልክ እውነተኛ አምላክ ነህ፣ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እግዚአብሔር ነህ ብሎ በመመስከሩ፣ ይህን የገለጸልህ የሰማይ አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም፡፡ አንድም መንፈስ ቅዱስ በወደደው አድሮ ምስጢርን ያናግራልና ይህን መንፈስ ገለጸልህ፡፡ በሌላው ሰው ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ካልተሰጠው በቀር ምሥጢርን ገልጾ አይናገርም አያስተምርም አይመሰክርምና ብፅዕ ነህ አንተ አለት ነህ ቤተክርስቲያኔን በዚህ ዓመት ላይ እሰራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም፡፡ (ዮሐ 1፡43 ፣ ዮሐ 6፡69)
ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም በሐዋርያው በፊሊጶስ የተጠመቀው ዓለት ነው፡፡ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ በማለት መስክሯል፡፡ (ሐዋ 8፡36)
ወንጌል የተጻፈውም የተተረጎመውም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር እንደሆነ አምነን እንድንድ ነው ፡፡ (ዮሐ 20፡31)
‹‹ጌታም በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያን እሰራለሁ የገሀነም ደጆች አይችሏትም›› ብሏል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ
1.  ቤተክርስቲያን ማናት
2.  የገሀነም ደጆች የተባሉት እነማን ናቸው?
3.  ለምን የገሀነም ደጆች አይችሏትም ተባለ
የሚለውን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡
1. ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ስለ ሦስት ነገሮች የተነገረ ሲሆን፡-
ሀ/ እያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን ነው
የተሠራንበት ዓለቱም ክርስቶስ ነው፡፡ በማቴ 7፡24 ላይ ‹‹ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል›› ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ የሚያምን፣ ልጅነትንም ገንዘብ የሚያደርግ ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡
‹‹ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያን ቤት ገፋው በዓለት ላይም ስለተመሠረተ አልወደቀም›› (ማቴ 7፡25)
ዝናብ የተባለ ከአላውያን ከከሃዲያን ነገስታት የሚመጣ መከራ፣ ሰይፍ ነው ፡፡ ጎርፍ የተባለውም የስደትና የመገፋት የመንገላታት ጎርፍ ነው፣ ነፋስ የተባለ የጥርጥር የክህደት ነፋስ ነው፡፡ ብዙዎች በሚዘንበው ዝናብ ተሰናክለው በጎርፍና በነፋስ ተወስደዋል፡፡ (ኤፌ 4፡14)
በዚህ ዓለት ላይም ስላልተሠሩ ተሰናክለውበታል፣ ተፍገምግመው ወድቀዋል፣ ንቀውታል አቃለውታል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹እነሆ በጽዮን የከበረ ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ የተፈተነውንም የከበረውን መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም›› (ኢሳ 28፡16)
ይህ ዓለት ጽዮን ከተባለችው ከተመረጠችው ከድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለቱ የተመረጠ፣ የከበረ፣ የተፈተነ ነውር ነቀፋ የሌለበት በባሕርይው ንጹህ የሆነ በመለኮቱ ሞት፣ በመንግስቱ ኅልፈት፣ በስልጣኑ ሽረት የሌለበት ነው፡፡
እኛ እንደ ክርስቲያንነታችን በዚህ ዓለት እናምናለን የባሕሪ አምላክ ፈጣሪ ነው ብለን አምነናል፡፡ በልጅነት ክብር አይተነዋል በሜሮን ታትመናል በሥጋ ወደሙ ከብረናል ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ከማይጠፋ ዘር ዳግም ተወልደናል፡፡
‹‹ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ የእንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ›› መዝ 117፡22 ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ግንበኞች የተባሉት ቤተ አይሁድ ጸሕፍት ፈሪሳውያን ቃሉ ሞልቶናል እናውቃለን የሚሉ የሕጉ ባለሙያዎች ግን እነርሱ ነበሩ ነገር ግን የከበረውን የተወደደውን የማዕዘን ራስ ድንጋይ ‹‹ፍጡር (የዮሴፍ ልጅ)፣ በአጋንንት አለቃ አጋንንት የሚያወጣ ብለው ጣሉት ተሰናከሉበት›› ያለ እርሱ ግን መሠረት የለም ያለ ክርስቶስ ክርስትናም ሆነ ክርስቲያን የለምና፡፡
እኛ የዚህ የሕያው እግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን ስለዚህም ቤተክርስቲያን ነን (1ቆሮ 3፡16) ለዚያውም በመስቀሉ የተቀደስን በጥምቀት የከብርን በቤዛነት ቀን የታተምን የእግዚአብሔር መቅደሶች ክርስቲያኖች እኛ ነን፡፡
ለ/ ቤተመቅደስ ሕንፃው ቤተክርስቲያን ይባላል





ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ክብር የምንዘምርበት ስለተደረገልን ነገር ሁሉ ምስጋናን የምናቀርብበት ቅዳሴ የሚቀደስበት ማህሌትና ሰዓታት የሚቆምበትን ስብሐተ እግዚአብሔር የሚፈስበትን ቃሉ የሚነገርበት ቅዱስ ሥፍራ ከመሆኑ ባሻገር የተሰበረውን ልባችን የሚጠገንበት የተቆረጠው ተስፋ የሚቀጠልበት እንባችን የሚታበስበት ሐዘናችን ወደ ደስታ ለቅሶአችን ወደ ሳቅ የሚቀየርበት እንቆቅልሻችን የሚፈታበት መርገማችን የሚሻርበት የአመፃ መዝገባችንም የሚገለበጥበት የጸጋው ግምጃ ቤት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ የፈቀደው እግዚአብሔር ሲሆን የቤተመቅደስ (የቤተ ክርስቲያን) መሠረቱም ሆነ ጉልላቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ኤፌ 5፡21 ፣ ዘጸ 25፡8) ቤተክርስቲያን በገጠርም ትሠራ በከተማ፣ በሕንፃም ትሠራ በአፈር ክብሯ አንድ ነው እሱም ክርስቶስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ደብተራ ድንኳን ነበረች ከዚያም ቤተመቅደስ በዘሩባቤል ዘመን 46 ዘመን ፈጅቶ ተሠራ፡፡ በአዲስ ኪዳንም ሰኔ 20 ቀን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሣሪያ ከሦስት ድንጋዮች ቤተመቅደስን መስርቶ ሰኔ 21 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የከበረበት ዕለት ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ድንጋይ ቤተመቅደስ አነፀ ሲባል የሚከብዳቸው የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ክርስቶስ የሁሉ ፈጣሪና አስገኚ በመሆኑ እኛንስ ከምድር አፈር አበጃጅቶ የሕይወትን እስትንፋስ የሰጠን፣ ዓለምንስ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የሠራ እርሱ አይደለ፣ ለእሱ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ (ዘፍ 18፡14)
ደግሞስ አይደለም ፈጣሪ ቅዱሳኑ እነ ቅዱስ ላሊበላ ከአንድ ድንጋይ 11 አቢያተ ክርስቲያናትን አንጸው የለ እንዴ ለዚያውም አለም ገና ባልሰለጠነበት ዘመን የኢትዮጵያ የሥልጣኔ አሻራ የሆነው ቤተመቅደስ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንéEል፡፡
በመሆኑም ጌታችን ከሦስት ድንጋዮች ቤተክርስቲያንን ሠራ ከዚያም በኋላ ሌሎች አቢያተ ክርስቲያናት ተሠሩ እነዚህም የበረከት የምስጋና ሥፍራ ናቸው፡፡ (መዝ 64፡4)
ሐ/ ቤተክርስቲያን የምዕመናን አንድነት የምዕመናን ህብረት ነው፡፡
‹‹ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን›› እንዲል ጸሎተ ሐይማኖት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች 12ቱ ደቀመዛሙርት፣ 36ቱ ቅዱሳት አንዕስት፣ 72ቱ አርድዕት ነበሩ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለ120ው በወረደ ጊዜ 3000 የሚያህሉ ነፍሳት (ክርስቲያኖች) በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት አመኑ ከዚያም በኋላ በሐዋርያት ስብከት 5000 የሚያህል ተጨምሮ በአጠቃላይ የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን 8000 የሚያህሉ ነበሩ፡፡ (ሐዋ 14፡27) ማህበረ ምዕመናኑን ቤተክርስቲያን እያለ ይጠራቸው እንደነበር ቅድስ ሉቃስ ‹‹አቢያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር በቁጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር›› (በሐዋ 16፡5) ላይ መዝግቦልናል፡፡





ስለቤተክርስቲያን ይህን ያህል ካልን ጌታ የገሀነም ደጆች ያላቸው ምን እንደሆኑ እንመልከት፡፡
ሀ/ ዲያብሎስና ሠራዊቱ
ቤተክርስቲያንን የሚያውክ የገሀነም ደጅ የተባለ የጥፋ ልጅ ቤተክርስቲያንን የሚበጠብጥ ሠላም የሚነሣ ዲያብሎስ ነው፡፡ በመጽሐፍ ‹‹ለክፉዎች ሠላም የላቸውም ይላል አምላኬ›› (ኢሳ 57፡21) ተብሎ እንደተጻፈ ዲያብሎስ የቤተክርስቲያን ዋንኛ ጠላት ነው፡፡
ዘወትር ሊያውክና ሊበጠብጥ ይዞራል (1ጴጥ 5፡7) ነገር ግን ቤተክርስቲያን በዓለቱ ላይ ስለተሠራች አይችላትም፡፡ ጌታችን በወንጌል ‹‹ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ›› (ሉቃ 22፡31) በማለት ሰላም ሊነሣ ቤተክርስቲያንን ሊያውክ ዘወትር እንደማያንቀላፋ ነገር ግን በእነሱ ላይ ኀይል እንደሌለው ነግሯቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ‹‹ዲያብሎስ ቤተክርስቲያንን ተዋጋ ቀስቱን ጨረሰ ዝናሩን አራገፈ ነገር ግን ቤተክርስቲያንን ሊጎዳት አልቻለም፣ ሰውን ታግለህ ማሸነፍ ትችል ይሆናል ቤተክርስቲያንን ግን ማሸነፍ አትችልም›› በማለት የገሀነም ደጆች የተባሉ ዲያብሎስና ሠራዊቱ እንደማችሏት አስተምሯል፡፡
ለ/ አህዛብና ዓላውያን ነገስታት
አሕዛብና ዓላውያን ነገሥታት የገሀነም ደጆች የጥፋት መልዕክተኞች የዲያብሎስ የግብር ልጆች ናቸው፡፡
አህዛብ በመግደልና በማጥፋት ያምናሉ (ፊሊ 3፡19) በተለይ ቤተክርስቲያን የተባሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ሰላም ይነሣሉ ያውካሉ፣ ‹‹በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች ዕረፍትም አላገኘችም›› (ሰ.ኤር 1፡3) ተብሎ እንደተጻፈ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ጨምሮ ብዙ ክርስቲያኖች በአሕዛብ ሰይፍ ሰማዕት ሆነዋል፡፡ በተለይም ከ4ኛው እስከ 4ኛ መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ዓላውያን ነገስታት በቤተክርስቲያን ላይ ጽኑ ፈተና ስላመጡ ቤተክርስቲያን በስደት በካታኮምብ እና በግበበ ምድር በዋሻ ለመኖር ተገደደች፡፡
ከዚህም የተነሣ ይህ ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ተብሏል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ዕለት ዕለት ትበዛ ነበረ እንጂ አልጠፋችም የገሀነም ደጆች አይችሏትምና በሀገራችንም በኢትዮጵያ ከዮዲት ጉዲት እስከ ግራኝ መሐመድ ዓላውያንና አሕዛብ በቤተክርስቲያን ላይ ተነስተው ተፈታትነዋታል፡፡ አሁንም የጥፋት መረባቸውን በመዘርጋት አቢያተ ክርስቲያናትን ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል ነገር ግን ቤተክርስቲንን አላሸነፏትም፡፡
ሐ/ መናፍቃን ተጠራጣሪዎች ሐሳውያን
እነዚህ በዘመነ ነቢያት ሐሳውያን በዘመነ ሐዋርያት ከሀዲያን፣ በዘመነ ሊቃውንት መናፍቃን ለቤተክርስቲያን የገሀነም ደጆች ናቸው፡፡ (2ቆሮ 11፡13)
የሃይማኖታችንን ሕግና ሥርዓት በመጠበቅ እንደ ቸርነቱ የምንወርሳትን ሰማያዊ ርስት እንዳናገኝ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት የመስቀሉን ኀይል በልባችን ከሞላችልን በ40ና በ80 ቀን ተጠምቀን ልጅነትን ካገኘንበት ቤተክርስቲያን ሊያስወጡን ራሳቸውን ከእውነተኞች ጋር በማመሳሰል ኑፋቄያቸውን በመዝራት ቤተክርስቲያንን ስለሚያውኩ የገሀነም ደጆች ናቸው፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ሰይጣን የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና›› (2ቆሮ 11፡13) እንዲል እነዚህ የአምልኮት መልክ አላቸው ኀይሉን ግን ክደዋል፡፡ የወንጌል ቃል ተከድኖባቸዋል (2ጢሞ 3፡6) ብዙዎችን በሐሰት ትምህርታቸው አጥምደዋል ስተው አስተዋል ‹‹እውቀት አለን ብለው አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና›› 1ጢሞ 6፡20
እነዚህ የትንቢት መፈጸሚያዎች መሆናቸውን ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት መዝግቦልናል ‹‹ከእኛ ዘንድ ወጡ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም ከእኛስ ወገን ቢሆኑ ከእኛ ጋራ ጸንተው በኖሩ ነበር ይገለጡ ዘንድ ወጡ›› ብሏልና (1ዮሐ 2፡18-20) እናስተውል፡፡
ጌታም በዘመነ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ዘመን እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢሏችሁ አትመኑ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፡፡ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን ያስታሉ፡፡ (ማቴ 24፡24)
መናፍቃን ሐሳውያን የጥፋት መረባቸውን ዘርግተው ሌት ተቀን ቢደክሙም እውነተኛይቱን ቤተክርስቲያን ግን ሊያጠፏት አይችሉም፡፡








በመሆኑም ቤተክርስቲያን በማይቻለውና በኀያሉ ላይ ስለተሰራች አይጥሏትም፣ በህያውና በሰማያዊው ላይ ስለታነጸች ምድራውያኑና ጊዜያውኑ አይችሏትም፣ በዘላለማዊው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ መሠረትነት ላይ ስለተገነባች የሲኦል ደጆች አያጠፏትም፡፡
ነገር ግን ጌታ ‹‹አይችሏትም›› አለ እንጂ አይቀርቧትም አላለም ቤተክርስቲያን በባሕር ውስጥ ያለች ታንኳ ወይም በዓለም ውስጥ ያለች ብቸኛ የሰላም ድንኳን ናት፡፡ ባሕር ወይም ዓለም በውስጧ ባሉ ባዕድ ፍጥረታትና በማዕበል እንደምትታወክ ቤተክርስቲያንም ከገሀነም ደጆች የተነሣ ጸጥታ የላትም ትታወካለች ትረበሻለች ‹‹ቀኑን በሙሉ ስላንተ እንገደላለን እንዲል›› መዝሙረኛው (መዝ 43፡22) ቤተክርስቲያንም ስለመሠረቷ ስለ ክርስቶስ ዘወትር ትገፋለች ጌታም ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ›› ነው ያለው፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያን ለ2000 ዓመታት በውጊያ ላይ ያለች ነገር ግን ያልተሸነፈች ወደፊትም የማትሸነፍ ታጋይ የማትጠፋ መቅረዝ የማትሰጥም ታንኳ ናት፡፡ ምክንያቱም መሠረቷ ጽኑው ዓለት ክርስቶስ አይችሏትም ብሏልና፡፡




No comments:

Post a Comment