ቤተሰብእ ማለት በቅዱስ ጋብቻ አማካይነት በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች (ወንድና ሴት) ግንኙነት የሚጀመረውና
ቁጥራቸው ይነስም ይብዛም የሚወለዱትን ልጆች ጨምሮ በጋራ የሚመሰረተው ማኅበር ነው፡፡
እንዲህ ዓይነት ቤተሰብእ የሚመሰረተው በቅዱስ ጋብቻ በሥጋውና ደሙ አማካኝነት ነው ይህም የጋብቻ ቡራኬና ጸሎት የሚፈጸመው አምላካችን እግዚአብሔር በሥነ-ፍጥረት
ጊዜ ሰው እንዲበዛ ቅዱስ ፈቃዱ ስለሆነ ለመባዛቱም ምክንያት የሚሆነው የወንድና የሴት ግንኙነት ሲኖር መሆኑን በማረጋገጥ አዳምና
ሔዋንን ፈጥሮ እንዲህ ሲል የፈጸመውን የመጀመሪያ የተክሊል ጸሎትና ቡራኬ መነሻ በማድረግ ነው ‹‹እግዚአብሔርም ሰውን ፈጠረ በመልኩ
በእግዚአብሔር መልክ ፈጠራቸው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው እግዚአብሔርም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት የባሕሩንም አሣ የሰማዩንም
ወፍ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሰውን እንሰሳ ሁሉ ግዙ›› ዘፍ 1፡27
ይህን ቅዱስና አምላካዊ ቃል መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ አንድ ወንድና አንዲት
ሴት ብቻ ተስማምተው በሚያደርጉት ጋብቻ ጊዜ ቡራኬውን ታስተላልፋለች፡፡ ከዚህ ጸሎትና ቡራኬ በኋላ ባልና ሚስት ምንም በተፈጥሮአቸው
በፆታቸውም ሁለት መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም አንድ አካል እንጂ ሁለት አይባሉም፡፡ ይህንም ጌታችን በወንጌል ‹‹ስለዚህም ሰው አባቱንና
እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› ማቴ 19፡5 በማለት አስረግጦ አስተምሯል፡፡
መልካም ቤተሰብእም የሚባለው አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት አንዲት ሴትም ለአንድ ወንድ ሁነው በሚጋቡት
ጋብቻ የተመሠረተው ጋብቻ ነው፡፡ ይህንንም ሲያጸና ሐዋርያው ‹‹ነገር ግን ስለዝሙት ጠንቅ ሁሉ ለእያንዳንዱ ሚስት ትኑረው ለሴቲቱም
ባል ይኑራት›› (1ቆሮ 6፡2) በማለት ጽፎአል፡፡
ከዚህ ውጪ አንድ ወንድ ብዙ ሴቶች ሊኖሩት አይቻልም አይገባምም አንዲት ሴትም ብዙ ወንዶች ሊኖሯት
አይቻልም አይገባምም፡፡ ለዚህም ወንድና ሴት እኩልነት ያላቸው ትክክልም የሆኑ በመሆናቸው ለአንድ ወንድ አንዲት ሴት ለአንዲት ሴትም
አንድ ወንድ ብቻ እንዲሆን አምላክ በመፍቀዱ በመጀመሪያው ፍጥረት ጊዜ አዳምና ሔዋንን ብቻ ፈጠረ፡፡ ለዚህም የመጀመሪያው ሰው እየተባለ
የሚጠራው አዳም ረዳት ትሆነው ዘንድ የተሰጠችው ሴት አንዲት ብቻ ናት እርሷም ከሩቅ የመጣች ባዕድም ሳትሆን ከጎኑ አጥንት እንድትፈጠር
አምላክ ፈቀደ ‹‹ለአዳም ግን በአጠገቡ የምትሆን ረዳት የምትስማማውን አላገኘለትም ነበር እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍ
ጣለበት አንቀላፋም ከጎኑም አጥንት ወስዶ ሥፍራውን ሥጋ መላበት እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት
ወደ አዳምም አመጣት አዳምም ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል አለ››
(ዘፍ 2፡20-23) በዚህም መሠረት ወንድና ሴት በተቀደሰ አላማ በተባረከም ጋብቻ ስለተሳሰሩ አንድ ናቸው፡፡ ሁለቱም የእግዚአብሔር
የእጁ ሥራ ስለሆኑ እኩል ናቸው ለተቀደሰም አላማ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ወንድ የእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ሆኖ እንደተፈጠረ ከዚያውም
ሥጋ ከዚያውም አጥንት ሴቷ የተፈጠረች እንደመሆኗ እርሷም የእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ናት፡፡
በሰው ነገድ መካከል ወንድ ወይም ሴት በማለት ጾታውን ምክንያት በማድረግ ልጅ ሽማግሌም በማለት ፆታን
ዕድሜን ምክንያት በማድረግ ወይም ጎሣንና ቀለምን ምክንያት በማድረግ ልዩነት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
እንዲህ ዓይነቱን የተሣሣተ አመለካከት በመቃወም ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በዚያም አይሁዳዊ የለም አረማዊም
ባሪያም የሰው ልጅም ወንድም ሴትም ልዩነት የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁና›› ገላ 3፡28 በማለት አስተምሮአል፡፡
የክርስትና ሃይማኖት የወንድንና ሴትን እኩልነት የሚሰብክ በትክክልም ለሰው ነገድ ጠቃሚ የሆነ መመሪያን
የሚሰጥ ሃይማኖት ነው ማለት ወንዱም ሴቷም እኩል የሆነ መብት እንዳላቸው ተፈጥሯቸውም እኩል እንደሆነ ይሰብካልና፡፡
በሕዝባዊ ሕግ ግን እስካሁን ገና ጾታን ያላስተካከለበት አገር ወይም መንግስት እንዳለ የታወቀ ነው፡፡
የክርስትና ሃይማኖት ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ጀምሮ ባልና ሚስት አንድ ናቸው እኩልም ናቸው በማለት ሲነገር በሥራም
ሲገለጥ እስከዚህ ድረስ ደርሷል፡፡
ቤተሰብእ በመንፈሳዊ ፍቅርና በበጎ ፈቃድ ይመሠረታል፣ ሀብቱና ንብረቱ ሌላውም ሁሉ በኋላ የሚገኝ የሚቀጥልም
እንጂ የቤተሰብእ መሠረታዊ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከባልና ሚስት ስምምነትና ፈቃድ በኋላ ጋብቻው በቤተክርስቲያን ቡራኬና ጸሎት በቅዱስ
ሥጋውና ደሙ መፈጸም አለበት፡፡ የጸሎቱም ውጤት የማይታዋወቁ ወገኖች ከመተዋወቅ ደረጃ በላይ አልፎ አንድ አካል እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
የተለያዩ ሁለት ጾታዎች አንድነታቸው ይጸናል እንደ አንድ ቃል ተናጋሪዎች እንደ አንድ ልብ መካሪዎች
ይሆናሉ፡፡ ልዩነት ወይም ሁለትነት ይጠፋል፡፡
ቤተክርስቲያን ከቅርብ ዘመድ ጋር ጋብቻ መፈጸምን ትከለክላለች፣ ምክንያቱም መንፈሳዊው ጋብቻ ባዕዱን
ዘመድ ያደርጋል፣ የራቀውን ያቀርባል የተለያየውንም አንድ ያደርጋልና ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ጸሎተ ጋብቻ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ያሰጣል፣
ያልተገለጠና የረቀቀ ምስጢር አለው ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹ይህ ምስጢር ታላቅ ነው እኔ ግን ስለክርስቶስና ስለቤተክርስቲያን
እናገራለሁ›› በማለት አስተምሯል፡፡ (ኤፌ 5፡32) የጋብቻው መንፈሳዊ ዓላማ ለሥጋዊ ግንኙነታቸውና ሕይወታቸው ብሩህ ተስፋን ይሰጣቸዋል፡፡
ጋብቻው ለዘላለም የማይፈታ መሆን አለበት በጋብቻ ጊዜ በቤተክርስቲያን የሚተላለፈው ጸሎትና ቡራኬ መንፈሳዊ
አገልግሎትም የሚሰጠው ጥቅም ባልና ሚስት በዚህ በምድራዊ ሕይወታቸው አንድ ሆነው በሚሰሩት በሚፈጽሙትም ተግባር ሁሉ ለጊዜው አንድነትን
መስማማትን በኋላ ደግሞ ሰማያዊ ክብርን ያገኛሉ ሰማያዊ አክሊልንም ይቀዳጃሉ ‹‹ጋብቻ በትንሽ በትልቁ በሰዎች ጣልቃ ገብነት በፈተና
የማይፈታ ዘላለማዊ ምስጢር መሆኑን ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ በወንጌል ላይ ‹‹እንግዲህ ሁለት አይደሉም እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን
ሰው አይለየውም›› ሲል ባልና ሚስት ለመለያየት የማይችሉ መሆናቸውን›› ገልጾአል፡፡ (ማቴ 19፡6) እንግዲህ ባልና ሚስትን ሊለይ
ሊያፋታም የሚችል ከቶ የለም ይህንንም ለማድረግ ከሰው ወገን ባይኖርም ሰይጣን በሁለቱ መካከል እየገባ ይለያያል ጋብቻንም ያፈርሳል፡፡
እውነተኛ ክርስቲያን ግን ይህን አውቆ ሰይጣንን መቋቋም የክርስቶስንም ትምህርትና ሕግ መጠበቅ አለበት፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታን ትምህርት ተከትሎ ጋብቻ የማይፈታ ምስጢር መሆኑን እንዲህ ሲል ይናገራል ‹‹የተጋቡትን ግን አዝዛችኋለሁ
እኔ አይደለሁም ጌታ እንጂ ሴት ባሏን እንዳትፈታ ብትፈታውም ሳታገባ ትቀመጥ ወይም ከባልዋ ጋር ትታረቅ ወንድም ሚስቱን አይፍታ››
(1ቆሮ 7፡10-11) ምናልባት አንደኛው ወገን በሞት ቢለይ ቋሚው እንደገና የማግባት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይህንም የመሰለ ሁለተኛ
የሞራል ሞት አንደኛውን ወገን ያገኘው እንደሆነ ማለት ዝሙት የሠራ የጋብቻውንም እምነት ያፈረሰ እንደሆነ ንፁሑ ወገን ሌላ የማግባት
እድል ይኖረዋል በመፍታት ምክንያት ግን እንደገና ማግባት ክልክል ነው ጋብቻው እንደ ዝሙት ይቆጠራልና፡፡
ባልና ሚስት እንደ አንድ አካል ሁነው በአንድነት ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታ አለባቸው እንዲሁም ባል ለሚስቱ
ሚስትም ለባሏ በየግላቸው ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታ አለ፡፡ ባልና ሚስቱ እንደገና በአንድነት ሁነው ለልጆቻቸው፣ ልጆቻቸውም ለእርሱ
ሊፈጽሙት የሚገባ ግዴታ አለ፡፡
ሀ/ ባልና ሚስት በአንድነት የሚፈጽሙት ግዴታ ጋብቻ ክቡር መኝታውም ንጹህና ቅዱስ ከመሆኑም ባሻገር
ዓላማና ግብ አለው (ዕብ 13፡4)
1.
ዘርን ለማትረፍ ምትክንም ለመተው ነው ማንኛውም
ፍጥረት እንዲበዛ እንዲራባም የፈቀደ አምላ የሰውም ወገን እንዲበዛ እንዲራባም ፈቅዷል፡፡ ለመብዛትና ለመራባት ምክንያት የሚሆነው
የሁለት ጾታ ግንኙነት ወይም ጋብቻ ነው፡፡
2.
ለመረዳዳት የሁለቱ ጾታ ግንኙነት ወይም ጋብቻ
ዋናው ዓላማ ለመረዳዳት ነው ይኸውም ወንዱ የሴቷን፣ ሴቷም የወንዱን ችግር በአንድነት ሆነው ለማስወገድ ነው ወንድ የሚችለውን ሴቷ
አትችለውም፣ ሴቷ የምትችለውን ወንዱ አይችለውም ይህም ከሆነ ችግር በሁለቱም ላይ ያንዣብብባቸዋል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዳይደርስባቸው በአንድነት ሁነው ችግራቸውን ያስወግዳሉ፣ ዕርዳታ ይበረካከታሉ
አምላክ ወንድ ብቻውን እንዲኖር እንዲቸገርም አልፈቀደም ስለዚህ ረዳቱን ሔዋንን ፈጠረለት፣ ሴቷም ብቻዋን እንድትኖር ችግርም እንዲደርስባት
አልፈቀደም ስለዚህ አዳምን ፈጠረላት እንግዲህ ከዚህ የተነሣ ጋብቻ አምላካዊ ትዕዛዝ ነው፡፡ በሕገ ተፈጥሮም አስፈላጊ መሆኑ ታውቀ
ተረዳ፣ ግን ዓላማውን ሳይለቅ መፈጸም አለበት፡፡ (ዘፍ 2፡20-25)
3.
ከፈቲው ጾር ለመዳን፡- የሥጋ ጠባይ ወደ ባሕርየ
እንሰሳዊነት ያዘነብላል ስለዚህም በየጊዜው ወንድ ወደ ሴት ሴትም ወደ ወንድ ያተኩራል ፈተናም ይመጣባቸዋል ይፈተናሉ፡፡ ከዚህም
ሁሉ ለመዳን ወንዱ የምትሆነውን ሴት፣ ሴቷም የሚሆናትን ወንድ ያባሉ ወይም ይጋባሉ እንግዲህ ቤተሰብን መመሥረት ትዳርን መያዝ ባልና
ሚስት ሆኖ መኖር ቅዱስ ተግባር መሆኑን ክርስቲያን ሁሉ መገንዘብ አለበት፡፡ ይህም ሁሉ ሲሰራ ሲፈጸም ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ክብር
ተብሎ መደረግ አለበት ስለ ሁሉም የእግዚአብሔር ስም መመስገን አለበትና፡፡
4.
በማኅበር ለመኖር
ለማኅበራዊ ኑሮ ምሳሌ የሚሆን እንዲያውም መሠረት የሚሆነው ቤተሰብእ ነው፡፡ መልካሙ ቤተሰብእ ለማኅበራዊ
ኑሮ ብቻ መሠረት ሳይሆን ለትልቁም መንግስት ሳይቀር መሠረት ነው ትልቁ መንግስት ከትንሽ ቤተሰብእ ተነስቶ ይመሠረታልና፡፡ ስለዚህ
ቤሰተብ የተናወጠ ጸጥታም የሌለው ከሆነ መንግስትንም እንዲሁ ያሰጋዋል አስተማማኝነትም አይኖረውም፡፡
ሰው በማኅበር እንዲኖር ተፈጥሯል፣ ይህንም ማኅበራዊ ኑሮን እያንዳንዱ ሰው በቤተሰብእ ይጀምራል፡፡
የሰው ታላቅነቱ አዋቂነቱም የሚለካው ሥልጣኔውም እርምጃውም የሚታወቀው ከገለልተኝነት ወጥቶ በማኅበር መኖሩ የተፈጠረበትንም ዓላማ
በማጽናቱ ነው፡፡
ሰው ሁሉ በአንድነት ወይም በማኅበር፣ ሲኖር ልጆች አብረው ያድጋሉ፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን
አጽንተው ያድጋሉ የሰው አንድነቱ እኩልነቱ ይታወቃል፡፡ አባት ያበጀው ለልጅ ይበጃል እንደተባለው አባቶችና እናቶች በቤታቸው በጎረቤታቸው
ሰላምን ጸጥታን ሲይዙ ልጆች ካዩ እነሱም ይህንኑ ተከትለው ሰላምን አጽንተው ይኖራሉ፡፡
የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤት ትምህርት ቤት መሆን አለበት፣ ማለት ስለ ሀገር ፍቅርመ ስለ ወገን ክብር
ስለ ሰው ልጅ እኩልነት ስለ ትክክለኛ ፍትሕ ሲነገር ሲሰራ ይታያል ፣ በዚህን ጊዜ ልጆች ይከተላሉ በሥራም ይገልጣሉ፡፡
እንግዲህ ጋብቻ ይህን የመሰለ ዓላማ ስላለው ባልና ሚስት ተባብረው ለራሳቸው፣ ለቤታቸው ፣ለቤተሰባቸው
መሥራት መፈጸም አለባቸው፡፡
ከሁሉም በፊት፡-
ሀ/ ባልና ሚስት በመካከላቸው ፍጹም ፍቅርና ክብር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ባልና ሚስት አንዱ ሌላውን
ማክበር በፍጹም ፍቅር መዋደድ ግዴታቸው ነው፡፡ የመጀመሪያው የጋብቻው ዓላማ ይኽ መሆን አለበት፡፡ ጌታም በአምላካዊ ቃሉ ‹‹እንግዲህ
አንድ አካል ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም›› ያለው አንዱ ሌላውን እንዳያዋርድ እንዳይንቅ፣ እንዳይጠላ እንደ አካል እንደ አንድ
ነፍስ ሆነው እንዲኖሩ ያጠይቃል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰጠው ጸጋ ባልና ሚስቱን ሲመክር ‹‹ወንድ ለሴቲቱ የሚገባትን ፍቅር ይፈጽምላት
እንዲሁም ሴቲቱ ለወንዱ ታድርግ›› ይላል፡፡ (1ቆሮ 7፡13)
ለ/ መተማመን እንዲኖራቸው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎተ ተክሊል (ቁርባን) ጊዜ ሁለቱም ወገኖች የሰጡትን
ቃል የገቡትንም ኪዳን ጠብቆ ጋብቻውን አክብሮ መኖር ግዴታቸው ነው፡፡
ሐ/ ተረዳድቶ መኖር፡- አንዱ የውስጡን ሌላው ደግሞ የውጭውን ተግባር እንዲፈጽም እንዲሁም አንዱ የሚችለውን
ያም የሚችለውን ሲሰራ ኑሯቸው ይደረጃል፣ ሕይወታቸውም ይጠብቃልና ፍቅርና ሠላምም ይመሰረታል፡፡
መ/ ልጆችን አብሮ ማሳደግ ከባልና ከሚስት የኅብረት ግዴታ አንዱ ልጆችን አብሮ በሚገባ ማሳደግ ነው፣
ማለትም ሴት ስትወልድ ያንቺ ናት ወንድ ሲወልድ ያንተ ነው ሳይባባሉ ሁሉም በሁለቱ አማካይነት የመጡ መሆናቸውን አውቆ ተረዳድቶ
ማሳደግ ግዴታ ነው፡፡
ሠ/ ቤቱን በኅብረት ማስተዳደር ‹‹የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል›› እንዲሉ አበው የአንቺ ቤት ነው
የአንተ ቤት ነው ሳይሉ ባልና ሚስት ማስተዳደር ግዴታቸው ነው፡፡
No comments:
Post a Comment