እንኳን ለዓብይ ጾም አደረሳችሁ
ጾምን እንጹም ባልንጀራችን እንውደድ
‹‹እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኀታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኩሉ ገድል ሠናይት››
ጾም የጸሎት እናት የአርምሞ እህት የዕንባ ምንጭና የመልካም ገድል ሁሉ ጥንተ መሠረት ናት
ባሕረ ጥበባትና ስንዱ እመቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል አንዱ የሒሳብ ስሌት ሰርታ የዘመን መቁጠሪያ ሳይንስን (ባሕረ ሐሳብን)
ቀምራ አበቅቴና መጥቅን ለይታ የአጿማትና የበዓላትን ዕለታት ወስና ለትውልድ ማስተለለፏ
ነው፡፡ በመሆኑም ዘወትር በየዓመቱ ሰባቱን የአዋጅ አጽዋማት ታውጃለች፣ ከነዚህም መካከል አንዱና ርዕሰ አጽዋማት የሆነው የዓብይ ጾም
(የጌታ ጾም) ነው፡፡ በቤተከርስቲያናችን ቀኖና መሠረት እምነት ጾም ጸሎትና ምጽዋት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ከመሆናቸውም
ባሻገር ጾም ጸሎትና ምጽዋት እንደ ጣራና ግርግዳ የመልካም ሥራ አበጋዞች ናቸው፡፡ እምነት በመሠረትነቱ እንዲጸና እንዲያድግና ሥራ
እንዲሠራ ጾም ጸሎትና ምጽዋት ያስፈልጋሉ፡፡ ጾምም ከእምነትና ከጸሎት ጋር ሲሆን ድንቅ ሥራ ያሰራል ይህ ከሆነ ዘንድ ደግሞ በጎ
ሥራን ሳይሰሩ ፍቅርን ሳይዙ ምህረትንና ይቅርታን ሳያደርጉ እጾማለሁ ማለት የረሃብ አድማ እንጂ ክርስቲያናዊ ጾም አይደለም፡፡