Thursday, January 5, 2017

ባል ግን የሚስቱ ራስና የቤተሰቡ ኃላፊ ነው።

Image result for ethiopian christian wed picture

ይህንን ቃል አስቀድሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሜሮን ለከበሩት ለቤዛነት ቀንም ለተጠሩት ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የጻፈው ሲሆን በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚኖሩት እንደ እግዚአብሔርም ፈቃድ ለተጠሩት እግዚአብሔርን እናምናለን ለሚሉት ክርስቲያኖች ሁሉ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ተመዝግቧል። ባል ቤተሰቡን ለማስተዳደርና ኃላፊነትን ለመሸከም ትዕግስትና ጠንካራ ትከሻ ሊኖረው ይገባል። በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን በባህላችንና በኅብረተሰባችንም ዘንድ ቢሆን እንደሚታወቀው ባል የቤተሰብ ኃላፊና አስተዳዳሪ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡም ሆነ ለማህበረሰቡ አርአያና ምሳሌ እንደ ትልቅ ስዕልም የሚታይ ነው። የባል ኃላፊነት እንደ አባትም ቢሆን ከመጋቢነቱና ከኃላፊነቱ ባሻገር ሌላ ትልቅ ሚና ያለው ሲሆን ይኽውም ልጆች አባታቸውን የሚመለከቱት እንደ ፈጣሪያቸው እንደ እግዚአብሔር ነው ፤ለምን ቢባል እግዚአብሔር ለፈጠራቸው ፍጥረታት በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ እንዲመግብ አባትም እንጅ ቆላ ወጥቶ ደጋ ወርዶ ለፍቶ ሠርቶ ቤተሰቡን ይመግባል ያስተዳድራልና። እግዚአብሔር ከመጋቢነቱ ለፍጥረቱ ካለው ፍቅር። የተነሳ እንዲከበርና እንዲፈራ አባትም እንዲሁ ነው። ከዚህም የተነሳ ልጆች በአባታቸው ላይ ቅሬታ ወይም ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ካላቸው ለእግዚአብሔር ለፈጣሪያቸውም ያላቸው አመለካከት ሊበላሽ ይችላል።
በመሆኑም ወንድ እንደ ባልም እንደ አባትም ለሚስቱም ሆነ ለልጆቹ አልፎም ለማህበረሰቡ ትልቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። እንዲያውም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ ባል ሚስቱን ወይም ቤተሰቡን ለማዳን ራሱንም መስዋዕት አድርጎ እስከማቅረብም ድረስ ቢሆን ሊሆን ይችላል።ሚስቶችም ለእግዚአብሔር እንደሚገዙ ለባሎቻቸው ደግሞ ይገዙ በትህትናም ይታዘዙ። እንዲህ በቀድሞው ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና። (፩ጴጥ ፫ ፣፯) ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ ባል የሚስቱ ራስ ነው፣ ክርስቶስ ነፍሱንም ሳይቀር ለቤተክርስቲያን እንደሰጠ ባሎችም ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው ይውዱ ዘንድ ግድ ነው።
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሚስት ለባሏ መገዛቷ በትህትና በጭምትነት መኖሯ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር የሚያሰጣት እንጅ በምንም ዓይነት መስፈርት ከባሏ በክብር ዝቅ የሚያደርጋት ወይም የበታች የምትሆን አይደለችም።
ነገር ግን በመጽሐፍ ሴቶች በነገር ሁሉ ደካሞች ናቸውና ፣ኅጢዓትም ቢሆን አስቀድሞ ከሔዋን ተገኝቷልና ሴት በዝግታ ትማር ተብሎ ስለተጻፈ በክርስቶስ ለሚኖሩት ክርስቲያን ሴቶች ለባሎቻቸው በፍቅርና በትህትና ቢገዙ በረከትን ያገኛሉ። ይህም ትእዛዝ የበላይና የበታች ፤የባሪያና የሎሌ ፤የገዥና የተገዥ የመሆን ሳይሆን የአልገግሎት ሕይወት ሊሆን ይገባል ። ባል በትዕግስት ሆኖ ወጥቶ ወርዶ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲመራ ለሚስቱም በትህትናና በፍቅር እየታዘዘ በክርስቶስ ሆኖ ትዳሩን ያገለግላል። ሚስትም ባሏን በነገር ሁሉ እያገዘች ና እየታዘዘች በክርስቶስ ቅፍር ሆና ትዳሯን ልታገለግል ይገባል።
የባልና የሚስት ጥምረት በፆታ ላይ የተመሠረተ የፉክክር ወይም የመዘባራት የሁለትዮሽ ሕይወት ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ያለ የመንፈስ አንድነትና ግንኙነት ፣ባልና ሚስት አንድ አካል ስለሆኑ እንደ የክርስቶስ የአካል ክፍል ስለሆነ አንዱ ለአንዱ ሲገዛ ለክርስቶስ የሚገዛ እንደሆነ ማስተዋል አለበት፤ ይህም ይሆን ዘንድ እርስ በራሳቸው በፍቅርና በመከባበር መገዛት አለባቸው።
በአጠቃላይ ጤናማና ጠንካራ ቤተሰብ ለመመሥረት የሁለቱም ኃላፊነት ቢሆንም ባል ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ። ቤተሰቡን በሥጋዊ ሠርቶ ከማስተዳደር ባገሻር በመንፈሳዊ ሕይወትም በርትቶ ማበርታት ይኖርበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዳስተማረ "ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንዲወርሱ አድርጋችሁ አክብሯቸው " እንዲል (፩ ጴጥ ፫፣፯)
ይህም ማለት በቃለ እግዚአብሔር ፣በጸሎተ ቅዳሴም ሆነ በማንኛውም መንፈሳዊ በዓላት ሁሉ አብሮ መሳተፍ ይገባል።
ከዚህም አልፎ ማንኛውንም ትላልቅ ውሳኔዎች በመመካከር አብሮ መወሰን እና የወደፊት ዕቅድን መሠረት መጣል ለትዳሩ ማደግ ጠቃሚ ነው።
እንደዚሁም ሁሉ ጠንካራ ሚስቶችም ለደካማ ባሎች ብርታት ሊሆኑ እንዲገባ ሲያሳስብ ሐዋርያው "እንግዲህ እናንተም ሚስቶች ሆይ ከባሎቻችሁ አንዳንዶች ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ በፍርሃት ያለውን ንጹሁን ኑሮአችሁን እየተመከለቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው " ይላል። (፩ ጴጥ፫ ፣ ፩) ይህም ማለት ፍቅር የማይገዛው ትህትና ና ትዕግስት የማያስተምረው የለምና ፤ በክርስቶስ ሆናችሁ በፍቅርና በትህትና እየተገዛችሁ አስተምሩአቸው ማለቱ ነው።
እግዚአብሔር በኪዳኑ ያጽናን አሜን።
ይቆየን።
-----------------------------------------------------------------------
መምህር ዲ/ን ቸርነት ይግረም
ታህሣሥ ፱ ፳፻፱ ዓ.ም

የሰዎችን ታሪክ የቀየረ ንጉሥ ልደት




ልዑለ ቃል በመባል የሚታወቀው ነቢዩ ኢሳይያስ የከበረውን ንጉሥ የአዳምን ዘር ሁሉ ናፍቆት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያለ ዘርአ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) የሚወለድበትን ዓመት በትንቢት መነጽር እያየ "ለድሆች የምስራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ፤ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ ፤ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ፤ የተወደደችውን የእግዚአብሔር ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽና ና ዘንድ ልኮኛል።"ኢሳ፷፩ ፣፪ እንዳለ ተላኪ ወልደ እግዚአብሔር በባሕርይ አባቱ ፈቃድ በራሱም በእግዚአብሔር ፈቃድ ታሪክ ለመቀየር ተወልዶ መገለጡን በትንቢት መጽሐፉ ላይ መዝግቦልናል።

የደጉ ሳምራዊ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናስብ ረጅም ዓመት ወደ ኋላ ተጉዘን ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመናት አስቆጥሮ የነበረው የነፍሳት ጩኽትና በቃላት ሊገልጹት የሚያዳግተው የነቢያትን ትንቢት መሠረት አድርገን እንደሆነ ልብ ይሏል።

የሰው ልጅ በአርያ ስላሴ ከሰባቱ ባሕርያት በእግዚአብሔር ገቢረ ዕድ ተፈጥሮ ገነትን ያህል ቦታ ቢሰጠውም ትዕዛዝን ሻረ ሕግ አፈረሰ ከእግዚአብሔርም ተጣላ፣ እርግማንንም ተረግሞ ፣ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ፍርድ ተፈርዶበት ወደ ምድረ ፋይድ ተጣለ።