Friday, December 7, 2012

ፃዲቁ አቡነ አረጋዊ ዘሮም

የፃዲቁ የአቡነ አረጋዊ አባት ይስሐቅ እናቱም እድና ይባላሉ፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያከብሩ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የተባረከ ልጅ ሰጣቸው እሱም አቡነ አረጋዊ ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ህገ ኦሪትን ትምህርተ ነቢያትንና ቅዱሳት መፃህፍትን እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ እሱም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየፀና እየበረታ አደገ፡፡
ሚስት ያገባ ዘንድ አጩለት፡፡ ፃዲቁ አባታችን አቡነ ዘሚካኤል/አረጋዊ/ ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ከብዙ ዘመን በኋላ ከሮም ወደ ግሪክ ሀገር አባ ጳኩሚስ የሚኖርበት ደውናስ ወደምትባል ገዳም የምንኩስናን ልብስ ይለብስ ዘንድ ሄደ፡፡ አባ ጳኩሚስንም አገኘው፡፡ አባ ጳኩሚስም ልጄ ሆይ አንተ የንጉስ ልጅ እንደ መሆንህ መጠን

የመንግስቱ ወራሽ ነህና መንኰሰህ ለመኖር ይቻልሃልን አለው፡፡ ብፁዕ አባታችንም አባቴ ሆይ የምድር መንግስት ኃላፊ ጠፊ ነው ነገር ግን የማታልፈውን የማትጠፋውን ዘለዓለማዊት መንግስት እወርስ ዘንድ እፈልጋለሁ አለው፡፡ በፈተናም ከፀና በኋላ በአስራ አራት ዓመቱ በአባ ጳኩሚስ እጅ የምንኩስናውን ልብስ ለበሰ፡፡ ከአመነኮሰውም በኋላ ስሙን ዘሚካኤል ብሎ ሰየመው፡፡ ከዚህም በኋላ በጾም በፀሎት ተጠምዶ ኖረ፡፡ ዕድሜው አነስተኛ ሲሆን ስለጥበቡ ስለምክሩና በእውቀቱ የልጅ አዋቂ ስለሆነ አረጋዊ ተባለ፡፡ የፃዲቁ ዜና በሀገሩ ተሰማ፡፡ እናቱ ንግስት እድና እርሱ ወዳለበት መጥታ መነኮሰች፡፡ በሴቶችም ገዳም ገብታ መኖር ጀመረች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም አስራት ይሆናት ዘንድ በቃል ኪዳን እንደሰጣት ከቅዱሳት መጽሐፍት አገኘ፡፡ በኢትዮጵያም ፍቅር ልቡ ተነደፈ፡፡ ማንም ሰው ሳያውቅበት ሁለት ደቀ መዝሙሮቹን ይዞ ቅዱስ ሚካኤል እየመራው ንጉሱና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሰ፡፡
በዚያም ጥቂት ቀን ከተቀመጠ በኋላ ተመልሶ ወደሮም ሄደ፡፡ በኢትዮጵያ በዓይኑ የተመለከተውን በጆሮ የሰማውን ሁሉ በዚያ ላሉ ወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ እርስ በራሳቸውም እኛም ወደዚህች ሀገር መሄድ አለብን ተባባሉ፡፡ ያላቸውን የመገልገያ ዕቃ ይዘው ከታቦቶቻቸውና ከካህናቶቻቸው ጋር ንዋየ ቅዱሳትና መጽሐፍቶችን ይዘው ከመሰል ወገኖቻቸው ጋር አባታችን ዘሚካኤል እየመራቸው ንጉሱና ጳጳሱ ካሉበት አክሱም ከተማ ደረሱ፡፡ ወንድማቸው ይስሐቅም በሮም ከነገሰ ከሰባት ዓመት በኋላ መንግስቱን ትቶ ወደ አክሱም መጣ፡፡ በዚያን ጊዜ እንደነሱ አመነኮሱት በአንዲት የፀሎት ቤት በአንድነት ሆነው ለፀሎት ተጠመዱ፡፡ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረጉ ቆዩ፡፡ መልአክት ዘወትር ባለመለየት ይጎበኟቸዋል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለፀ ይጎበኛቸው ነበር፡፡ እያንዳንዳቸውም የሃይማኖታቸውን ኃይል አሳዩ፡፡ ከነሱ መካከልም ተራራ ያፈለሱ፣ ባህሩን ከፍለው ደረቅ መንገድ ያደረጉ ፣ስንዴ ዘርተው ወዲያው ለዘጠኝ ሰዓት መስዋዕተ ቁርባን ያደረሱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች በውስጧም በመመላለሳቸው አውራጃዎቿና አደባባዮቿ ሁሉ ታደሱ፡፡ ማር 9፡23
አባታችን ዘሚካኤልም የበላይ ጠባቂያቸው ወይም መሪያቸው አደረጉት፡፡ ለየብቻቸው ለመኖር ተስማሙ፡፡ በዚያን ጊዜ መሪር እንባ እያነቡ ለየራሳቸው ተለያዩ፡፡ አባታችንንም ስሙን አረጋዊ ብለው ሰየሙት ብልህ አዋቂ ማለት ነው፡፡ አባታችንም ወደመረጠው ቦታ ሲሄድ ከዛፍ ጥላ ስር አረፈ፡፡ እስዋም እስከ ዛሬ ድረስ የቅድሳን ማረፊያ ሆኖ ትገኛለች፡፡ ቅድስት ቦታ ዳሞን ባያት ጊዜ ሶስት ጊዜ ሰገደ፡፡ በተራራዋ ስር ለመኖር ወደደ፡፡ ነገር ግን ወደ ተራራዋ መውጫ አላገኘም፡፡ ተመልሶ ወደ ሌላ ተራራ ሄዶ አማረጠ ነገር ግን እንደ ደብር ዳሞ የበረከት ቦታ አላገኘም፡፡ ተመልሶ ወደ ደብረ ዳሞ ሄደ፡፡ በዚያም የምንጭ ውሃ አገኘ፡፡ ውሃውን እየተንከባከበች የሴት መነኮሳቶችን ታስተዳድር ዘንድ እናቱ ቅድስት እድናን አስቀመጣት ይህችንም ደብረ በአተልሞ አላት ትርጓሜውም የእናቴ ማረፊያ ቤት ማለት ነው፡፡
ከዚያም ሲሄድ ጠፍጣፋ ድንጋይ አገኘና ከዚያ ላይ ትንሽ ምንጣፍ አነጠፈና ተቀመጠ፡፡ በትሩንም በድንጋይዋ ላይ አቆመ፡፡ በተነሳም ጊዜ ደቀመዝሙሩ ማቲያስ በትሩንና ምንጣፉን ባነሳው ጊዜ ያች ድንጋይ ቁመቷም ጎኗም ልክ በዚያች ምንጣፍ ዓይነት ቅርጽ አወጣች፡፡ የቀድሞ መልኳ ነጭ ሲሆን አሁን ግን የማይፋቅ የማይላጥ ቀይ ቀለም ሆኗል፡፡ ስለአባታችን አቡነ አረጋዊ ስለታላቅነቱና ስለክብሩ ከዚያ የደረሰ ሁሉ ይሳለሟታል፡፡
ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንገድ ሲሄድ ውሎ ከተራራ አጠገብ ወደ ታች የተንዠረገገች ሀረግ/ገመድ/ አገኘና በስሯ ሶስት መዓልት ሶስት ሌሊት ሲፀልይ ከቆየ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ እግዚአብሔር ያከበረህ ቅዱስ ሆይ ምን ያስጨንቅሃል አለው፡፡ አባታችንም ከዚህ ተራራ ላይ ወጥቼ ስለኃጢአቴ ይቅርታን እጠይቅህ ዘንድ እወዳለሁ አለው፡፡ ሊቀ መልአኩም ወደ ተራራው የምትወጣበትን እግዚአብሔር እስኪልክልህ ድረስ ጥቂት ጊዜ ታገስ አለው፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊ በተራራው ፍቅር ልቡ ስለተነደፈ አዘነ፡፡ አጥብቆም አለቀሰ፡፡የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ዳግመኛ መጥቶ አረጋዊ ሆይ አይዞህ አትፍራ ስልጣን ተሰጥቶሃል፡፡ በሐረጓ በስተቀኝ በኩል ባለችው ቦታ ተቀመጥ ወደ ተራራው ጫፍ ያወጣህ ዘንድ በገመድ ፋንታ ቁመቱ ስድሳ ክንድ የሆነ ታላቅ ዘንዶ እግዚአብሔር ይልክልሃል አለው፡፡ እሱም በጾም በፀሎት ሁለት ሱባኤ ወይም አስራ አራት ቀን በዚያ ተቀመጠ፡፡ የታዘዘውም ዘንዶ በሶስት ሰዓት መጣ በዘንዶው ጅራት ላይ ወጥቶ በቅጽበት ከተቀደሰው ተራራ ጫፍ ላይ ደረሰ፡፡ እንደደረሰም ሶስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ስለዚህም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሎ ተሰየመ፡፡በመሸም ጊዜ አነስተኛ ዳቦ አንስቶ ባረከ መብላትም ጀመረ፡፡ ዳቦዋ ግማሽ ስትሆን ጠገበ የዳቦውን ግማሽ አምሳል ለኋለኛው ትውልድ ምልክት ትሆን ዘንድ እንጨት ጠርቦ/ቀርጾ አስቀመጠ፡፡ ይህች ምልክት እስከዛሬ ድረስ አለች፡፡ ደቀ መዝሙሮቹም ከታች ወደ ላይ የሚወጡበትን መሰላል ሰሩ፡፡
ብፁዕ አባታችን አቡነ አረጋዊ መጠነኛ ቤት ሰራና አብሮ ይዞት የመጣውን ታቦት በውስጡ አስገባ፡፡ ስለቁርባኑ ወይም ስለመስዋዕቱ እግዚአብሔርን ለመነ፡፡ እግዚአብሔርም ልመናውን ሰመቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ መልአክት ከሰማይ ይዘውለት ወረዱ፡፡ ለመኖሪያውም ትንሽ በዓት አገኘ፡፡ በዚያም ያለምንም መኝታ በፀሎትና በስግደት በመትጋት ተቀመጠ፡፡በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚሰቃዩትን በፀሎቱ ኃይል ፈወሳቸው ያላመኑትን እያስተማረ አሳመናቸው ለዚያች ሀገር ብርሃን አበራላት፡፡ፊንሐስ የተባለ የሃማሪያው ንጉስ በናግራን ሀገር ያሉ ክርስቲያኖችን ገደለ፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱንም ሁሉ አቃጠለ፡፡ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ በናግራን አገር ስለተፈጁት ክርስቲያኖች መልዕክት ወደ ኢትዮጵያ/አክሱም/ ንጉስ ወደ አፄ ካሌብ ላከ፡፡ ንጉሱም ወደ አባታችን አቡነ አረጋዊ አባቴ ሆይ በፀሎትህ አስበኝ የፃድቅ ሰው ፀሎት ግዳጅ ትፈጽማለች ኃይልም ታሰጣለች በጠላት ላይም ድልን ታቀዳጃለች ብሎ ላከበት፡፡ አባታችንም እግዚአብሔር ይርዳህ አለው፡፡ አፄ ካሌብም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ፀለየ፡፡ ጦሩን አዘጋጅቶ ዘመተ በእግዚአብሔር ቸርነትና በአባታችን ፀሎት በድል አጠናቀቀ፡፡ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ አባ ጴንጠሌዎን ገዳም ገብቶ መነኮሰ፡፡ ኢትዮጵያዊው ንጉስ አፄ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረሃ ዋሻ አስራ ሁለት ዓመት በጾም በፀሎት በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ ግንቦት ሃያ ቀንም አረፈ፡፡ከዚያም የካሌብ ልጅ አፄ ገብረመስቀል ነገሰ ወደ አባታችንም ሄዶ ሀገሩንና ህዝቡን እንዲባርክ አጥብቆ ማለደው፡፡ አባታችንም እንደቃልህ ይደረግ አለው፡፡ መልሶም አፄ ገብረመስቀል አባታችን አቡነ አረጋዊን በየትኛውም ቦታ ላይ ቤተክርስቲያንህን አሳንፅ ዘንድ ትፈቅዳለህ አለው፡፡ አባታችንም ቤተክርስቲያን የሚሰራበትን ቦታ አሳየው ንጉሱ አፄ ገብረመስቀልም በተባለው ቦታ ላይ ቤተክርስቲያኑን አሳነፀ፡፡ በውስጡም በድንጋሌ ስጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም የተሰየመች በወርቅና በብር የተጌጠች ታቦት አስገባ፡፡ንጉስ አፄ ገብረመስቀል ከተራራው ላይ ሲወርድ ለቤተክርስቲያኑ ማሰሪያ የሆነውን መወጣጫ መሰላል ላፍርሰው ብሎ አባታችንን ጠየቀ አባታችንም አዎ አፍርሰው አትትወው ነገር ግን ስለዘንዶው ጅራት ፈንታ ሰዎች ይወጡበት ዘንድ ገመድ አብጅ አለው፡፡ ንጉሱም አባታችን አቡነ አረጋዊ እንዳዘዘው አደረገ፡፡ ስለዚህም ደብረ ደኃምሞ ተብሎ ተሰየመ፡፡
የአባታችንን የጻድቁን ዜና ሰምተው አስኬማ ያቀዳጃቸው ወይም ያመነኩሳቸው ዘንድ ወደ እርሱ ብዙዎች ይመጣሉ፡፡ ለመመንኮስ የወደደ ሁሉ በተራራው ግርጌ ወዳለች ወንዝ/ውሀ/ ወስደው ያጥቡታል ከዚያም ወደ ተራራው ያወጡትና ያመነኩሱታል፡፡ ያችም ወንዝ ወይም ውሃ ማየ ምርቃይ/መጠመቂያ/ ትባላለች፡፡ እስከዛሬም ድረስ በዚህ ስም እየተጠራች አለች፡፡ፃዲቁ አቡነ አረጋዊ በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ እናቱ እድና ጥር አራት ቀን አረፈች፡፡ አባታችን አቡነ አረጋዊ ባሰራላት አዲስ መቃብር ቀበራት፡፡ አቡነ አረጋዊ በዚሁ በደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ብዙዎችን የሃይማኖት ትምህርት አስተማረ፡፡ ልጆቹ እንደበዙ በተመለከተ ጊዜ በየወገናቸው አዛዥ ሾመላቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ከድካም ወደ እረፍት ከኃዘን ደስታ ወዳለበት ከአሣር ወደ ክብር ቦታ በታላቅ ደስታ እወስድህ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ፡፡ መታሰቢያህን ያደረገ በፀሎትህም የተማመነውን ሁሉ እኔ በመላአክት ፊት ሞገስን ባለሟልነትን እሰጠዋለሁ፣ በስምህ በተሰራው ቤተ መቅደስህ ውስጥ የፀለየ የለመነ ፈጥኜ ፀሎቱን እሰማዋለሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያንህን ለሰራ አስራ ሁለት የብርሃን አዳራሽ አዘጋጅለታለሁ፣ የገድልህን መጽሐፍ በመታመን በንጽህና አድርጎ በቤቱ ያስቀመጠ የወረርሽኝ በሽታ ወይም ቸነፈር በቤቱ አይገባም፡፡ ድንገተኛም የሰውና የእንስሳ ሞት አይደርስበትም የእህል ችግርም አይኖርበትም፣ ከሁሉም ይልቅ የሞት ጥላ አያርፍብህም መልአከ ሞትም ሊያስደነግጥህ አይችልም እንደ ነቢያቶቼ ኤልያስና ሄኖክ ትሰወራለህ ብሎ ብዙ ቃል ኪዳኖች ገባለት፡፡ አባታችንም ጌታ ሆይ መታሰቢያዬን ያደረገ የገድሌን መጽሐፍ የፃፈ በፀሎቴ የተማመነ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ አለው ጌታም እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ዳግመኛም በስምህ በተሰየመ ቤተክርስቲያን ሁሉ በዚያ የተቀበረ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡ እነዚህንም ሁሉ አስራት አድርጌ ሰጠሁህ አለው፡፡ ይህን ከነገረው በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አረገ፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊ ደቀ መዝሙሩ ማትያስን ጠርቶ ጌታችን ተገልጦ የሰጠውን ቃልኪዳንና ይህ መጽሐፍ ተጽፎ ለልጅ ልጅ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነገረውመዝ 111/112 ፡ 6 ወንድሞቹ ደቀ መዛሙርቶቹን እንዲሰበስብም አዘዘው፡፡ ማትያስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ አባታችን አቡነ አረጋዊም ከበዓቱ በመውጣት እንደተለመደው በመካከላቸው ተቀምጦ አስተማራቸው ቀጥሎም ከዛሬ ጀምሮ በስጋ አታዩኝም አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ከአባታችን እግር ስር ወድቀው መሪር እንባን አለቀሱ፡፡ ክቡር አባታችን አቡነ አረጋዊ አረጋጋቸው፡፡
ፃዲቁ አባታችን አቡነ አረጋዊ የእርጅና ዘመኑ ደረሰ፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሆነው፡፡ በጥቅምት 14 ቀንም ተሰወረ፡፡ በዚያም ከመቋሚያና ከመስቀል በስተቀር ምንም የተገኘ የለም፡፡
የአባታችን የአቡነ አረጋዊ ረዴትና በረከት ይደርብን!!!

No comments:

Post a Comment