የጌታችን የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሰው ልጆች መዳን መሠረት የተጣለበት፣ መላእክት በደስታ የዘመሩበት፣ በጨለማ ለነበረው ዓለም ብርሃነ የወጣበት ዲያብሎስ የተጨነቀበት ሰብአ ሰገል በደስታ የዘለሉበት ሰማያዊው አምላክ ስለ ሰው ልጆች ሰው ሆኖ ተወልዶ ከእናቱ ጡት ወተትን እየለመነ ያለቀሰበት ታላቅ እለት ነው፡፡
ስለዚህ በዓል ምንነት ትርጉምና ምስጢር ለመናገር ጥልቅ መንፈሳዋነትና ብሩህ የሆነ ውሳጣዊ ዓይን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ስለ ልደቱ መናገር በእኛ ከሚጻፍ ይልቅ እንዲህ ያለውን ብሩህ ዓይን ገንዘብ ያደረጉ ቅዱሳን አባቶች የተናገሩትና የጻፉት ቢቀርብ እንደሚሻል ግለጽ ነው፡፡ ስለዚህም ቀጥለን ቅዱስ ኤፍሬም እና ቅዱስ ያሬድ የጌታችንን ልደት አስመልክተው የተናገሩትን /ያዜሙትን/ መርጠናል፡፡
ጽሑፎቹ ሲነበቡ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ሊሉ እንደሚገባ ልንጠቁም እንወዳለን፡፡
1. በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ በዓላት በዚያ በበዓሉ የሚወሳው ድርጊት በተፈጸመበት ዕለት እንደተገኘን ሆነን ደስታና በረከትን የምናገኝባቸው ተፈጥሮአዊውን የጊዜ ዑደት አልፈን ወደ ኋላ የምንሻገርባቸው ድልድዮች ናቸው፡፡ የጌታችንን ልደትም ስናከብር ልክ እንደ ሰብአ ሰገልና እንደ እረኞቹ በቤተልሔም ዋሻ እንደተገኘን ሆነን ከመላእክትም ጋር እየዘመርን ነው፡፡
የእነዚህ የሁለት ቅዱሳትን አባቶች ድርሰቶችም ይህንን መልእክት የያዙ ናቸው፡፡ በንግግራቸው «ዛሬ» የሚለው ቃል ተደጋግሞ ይስተዋላል፡፡
ይህ «ዛሬ» የሚለው የበዓላት አከባበር ጽንሰ ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በቅዳሴ እና በሥጋ ወደሙ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ከጊዜ በላይ ሆነን ከእኛ በፊት በነበሩ ከቅዱሳን ማኅበር በሰማይ መላእክት ማኅበር ጋር ከዚህም በላይ በመሰዊያው ላይ ካለው ከክርስቶስ ጋር አንድ ላይ እንሆናለንና፡፡
2. ስለ ልደት በዓል ሲነገር ትልቁ ትኩረት መደረግ ያለበት የተደረገውን ነገር ማድነቅ ነው፡፡ የማይወሰነው አምላክ መወሰኑ፣ የሁሉ ባለቤት የሆነው ራቁቱን መሆኑ፣ የሁሉ ፈጣሪ መወለዱ፣ ጊዜ የማይወሰንለት ሕጻን መባሉ፣ ዕድሜን መቁጠር መጀመሩ እና ሌሎችም፡፡
የእነዚህ ቅዱሳን አባቶች ድርሰቶች አሁንም እንዲህ ያሉትን ድንቅ ነገሮች አጉልተው በማሳየት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
አምላካችን ልደቱን እነርሱ በተረዱትና ባወቁት መጠን አውቀነውና ተረድተነው በልደቱ ብርሃን እንድንደሰት ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ቅዱስ ያሬድ
ቅዱስ ያሬድ በስደስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ኢትዮጵያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ እና የዜማ ደራሲ ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን ዛሬም ድረስ ለአገልግሎት የምትጠቀምባቸውን የአገልግሎት መጻሕፍት በአብዛኛው ያዘጋጀው እርሱ ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ላሉት በዓላት እና አጽዋማት በቀኑና በጊዜያት ምስጋና የሚቀርብባቸውን መጻሕፍት እና ዜማ ደርሷል፡፡
ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ዋነኛው ድጓ የተባለው መጽሐፍ ነው፡፡ ቀጥሎ በዚህ መጽሐፍ ልደትን አስመልክቶ ያቀረባቸው ምስጋናዎች ቀርበዋል፡፡
• እምርሁቅ ብሔር እምጽኡ ሎቱ እምሃሁ ወርቀ ከርቤ ወሰሂነ፤ አስከበቶ እሙ ውስተ ጎለ እብን፤ ከደነቶ እሙ ቆድለ በለሶን፤ ወትቤሎ ስሙ መድኃኔ ዓለም
• ስብአ ሰገል ከሩቅ ሀገር እጅ መንሻውን ወርቅ፣ ከርቤ እና እጣን አመጡለት፡፡ እናቱ በድንጋይ በተሰራ ግርግም ላይ አስተኛቸው የበለስ ቅጠልም አለበሰችው ስሙንም መድኃኔ ዓለም አለችው፡፡
• እግዚእ እድ ወአንስት ወሕጻናት ከመ ይቤዙ ተወልደ ኖላዊ ሄር፤ ዘመርኤቶ ይረድእ ወአባግዒሁ ያድኀን
• መንጋውን የሚረዳ በጎቹንም የሚያድነው ቸር እረኛ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናት ያድን ዘንድ ተወለደ፡፡
• ነያ ዜና ንዜኑ ለዘየአምን፤ እስመ ተወልደ ለክሙ ዮም ምደኅን፣ አምላክ ዘይሠሪ ኀጢአተ ዓለም
• እነሆ ለሚያምን ሰው የምሰራችን እንናገራለን፤ ዛሬ የዓለምን ኀጢአት ይቅር የሚል /የሚያጠፋ/ መድኃኒትና አምላክ ተወልዶላችኋል
• በጎል ሰከበ፤ በአጽርቅት ተጠብለለ፤ ውስተ ማኀጸነ ድንግል ኀደረ፤ ዮም ተወልደ እግዚእ ወመድኀን ቤዛ ኩሉ ዓለም
• በግርግም ተኛ፤ በጨርቅም ተጠቀለለ በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፤ የዓለም መድኃኒት ጌታ ዛሬ ተወለደ፡፡
• ዮም በርህ ሠረቀ ለነ፤ ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ ማኀጸነ ድንግል ጾሮ፤ እንዘ አምላክ ውእቱ ኀደረ ወተገምረ፡፡
• ዛሬ ብርሃን ወጣ፤ ሰማይና ምድር የማይችለውን የድንግል ማኅፀን ተሸከመው፤ አምላክ ሲሆን በማኅፀን አደረ፡፡
• ዮም ፍስሃ ኮነ በዛቲ ዕለት፤ ተቤዘነ ኩልነ ዘእም ድንግል በዓልነ ዮም እሃውየ፤ ለነ ሣህልነ ዮም ተወልደ ለነ መድኃኒተ ነፍስነ፡፡
• ዛሬ በዚህች ዕለት ደሰታ ሆነ፤ ከእመቤታችን /በተወለደው/ ሁላችንም ተቤዥን፤ ወንድሞቼ ዛሬ በዓላችን ነው፤ ዛሬ ለኛ የይቅርታችን ዕለት ነው፤ የነፍሳችን መድኃኒት ዛሬ ተወለደ፡፡
• ዮምሰ አሃውየ ሠረቀ ለነ ብርሃን፤ ዮም ተወልደ ክርስቶስ እምድንግል፤ ዮም፤ ዮም ዮም ይትፌስሐ አድባረ ጽዮን፡፡
• ወንድሞቼ ዛሬ ብርሃን ወጣልን፤ ዛሬ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ ዛሬ ዛሬ ዛሬ የጽዮን ተራራዎች ደስ ይበላቸው
• ዮም እግዚአ ሰማያት ወምድር በጎል ሰከበ እሳት በአጽርቅት ተጠብለለ፤ ሀሊቦ ጠበወ፤ ዮም ዘይፀወርዎ ሱራፌል በክንፍ በከርሥ ተፀወሩ፤ ዘያሌዕሎ ለማዕበለ ባሕር ሐሊበ ጠበወ፤ ኢንክል ከቢቦቶ፣ በአርምሞ ናዕኩቶ፤ ንስግድ ሎቱ ለክርስቶስ
• ዛሬ የሰማይና የምድር ጌታ በግርግም ተኛ፤ እሳት በጨርቅ ተጠቀለለ፤ ወተትን ጠባ፤ ሱራፌል በክንፍ የሚሸከሙት ዛሬ በሆድ አደረ፤ የባሕርን ማዕበል ከፍ የሚያደርግው ወተትን ጠባ፤ እርሱን መክበብ /መድረስ ፣ መረዳት/ አንችልምና በዝምታ እናክብረው ለክርስቶስ እንስገድለት፡፡
• ይትፌሳሕ ሰማይ ወትትሃሰይ ምድር በብዙኀ ሰላም በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ ዮም ሠረቀ ለነ ብርሃን፡፡
• በክርስቶስ ልደት ሰማይና ምድር በብዙ ሰላም እጀግ ደስ ይበላቸው
• አንፈረዓፁ ሰብአ ሰገል ረኪቦሙ ሕፃነ፤ ለመድኃኒትነ መንክር ግርማሁ እምድኅረ ተወልደ ድንግልናሃ ተረክበ፤ እውነ ኮነ ልደቱ፤ ብርሃነ ኮነ ምጽአቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ
• ሰብአ ሰገል ሕጻኑን እግኝተው በደስታ ዘለሉ፤ የመድኃኒታችን ግርማው ድንቅ ነው፡፡ ከተወለደ በኋላ /የእናቱ/ ድንግልናዋ አልጠፋም፤ የመድኃኒታችን ልደቱ እውነት፤ መምጣቱም ብርሃን ሆነ፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም
ቅዱስ ኤፍሬም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሶርያ የነበረ የቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡ በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት ታላላቅ የነገረ መለኮት ምሁራን እና ጸሐፊዎች አንዱ ነው፡፡ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ድረስ የምትጠቀምበትን ዜማ የደረሰውም ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም እጅግ በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ስለ ጌታችን ልደት የደረሳቸው ከ40 በላይ መዝሙራት /Hymns on nativity/ ይገኙባቸዋል፡፡
በእነዚህ መዝሙራቱ የጌታችንን ልደትና በልደቱ የተገለጠውን የጌታችንን ትህትና እና የእመቤታችንን ክብር አጉልቶ ይጽፋል፡፡
ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ቀጥለው ቀርበዋል፤ የአባታችን በረከቱ ይደርብን፡፡
በእንተ ልደት /17ኛ መዝሙር/
1. እመቤታችን እንዲህ አለች፣ «የምሸከመው ሕጻን ተሸከመኝ፤ ዝቅ ብሎ በክንፎቹ መካከል አስቀመጠኝና ወደ ላይ /ወደ አየር/ በረረ፡፡ «ከፍታው እና ጥልቁ ሁሉ ይለጅሽ ነው» ብሎ ቃል ገባልኝ፡፡
2. «ጌታ» ብሎ የጠራውን ገብርኤልን እና በትህትና ያቀፈውን አረጋዊ አገልጋይ /ስምዖንን/ አየሁ፡፡ ሰብአ ሰገል ሲሰግዱ እና ሄሮድስም ንጉሱ መጥቷል ብሎ ሲሸበርም አየሁ፡፡
3. ሙሴ ይጠፋ ዘንድ ሕጻናት ሲያስገድል የነበረው ሰይጣን አሁንም ሕያው የሆነው ይሞት ዘንድ ወንድ ልጆችን ያስገድላል፡፡ ሰይጣን ወደ ይሁዳ ስለወጣ ወደ ግብጽ ብሸሽ ይሻለኛል፤ አዳኙን የሚያድነው /ሰይጣን/ ግራ ይጋባ ዘንድ፡፡
4. ሄዋን በድንግልናዋ ጊዜ የሃፍረትን ቅጠሎች ለበሰች፤ እናትህ ግን በድንግልናዋ ጊዜ ለሁሉ የሚበቃ የክብር ልብስ ለበሰች፡፡
5. በህሊናዋ እና በልቧ አንተ ያለህ ያቺ እናትህ የተባረከች ናት፡፡ ለአንተ ለንጉሱ ልጅ ቤተ መንግስት፤ ለአንተ ለሊቀ ካህናቱም ቅድስተ ቅዱሳን ሆናለችና፡፡
በእንተ ልደት /መዝሙር 18/
1. ሰዎች «ፀሐይ» ብለው በሚጠሩት ንጉስ /አውግስጦስ ቄሳር/ ዘመን ጌታ በእስራኤላውያን መካከል አበራ፤ የእውነተኛው ብርሃን መንግስትም ተመሠረተ፤ እርሱ በምድር ንጉስ በሰማይ ደግሞ ልጅ ነውና፤ የተመሰገነ ይሁን፡፡
2. ግብር ለመሰብሰብ ሰዎችን በመዘገበው /በጻፈው/ ንጉስ ዘመን መድኃኒታችን ሰዎችን በሕይወት መጽሐፍ ይጽፍ ይመዘግብ ዘንድ ተወለደ፡፡
3. በዚህ ምድር ሰላሳ ዓመታት ያህል በድህነት ቆየ፡፡ ወንድሞቼ ለእነዚህ ለጌታ ዓመታት ሁሉንም ዓይነት ምሥጋና እናቅርብ፡፡ ልደቱ የተመሰነ ይሁን፡፡
በእንተ ልደት /11ኛ መዝሙር/
1. ጌታ ሆይ፣ እናትህን እንዴት ብሎ /ምን ብሎ/ መጥራት እንዳለበት የሚያውቅ ማንም የለም፡፡ «ድንግል» ብሎ እንዳይጠራት ልጅ አላት፤ «ያገባች» እንዳይላትም ማንም /በግብር/ ያወቃት የለም፡፡ ነገር ግን እናትህ እንዲህ ልትገለጽ የማትችል ከሆነች፣ አንተን ሊገልጽህ /ሊያውቅህ/ የሚችል ማን ነው? ሁሉ ነገር በፊትህ ቀላል ለሆነው ለሁሉም ጌታ ለአንተ ምሥጋና ይገባል፡፡
2. እርሷ ብቻዋን እናትህ ነች፤ ከሁሉም /ከክርስቲያኖች/ ሁሉ ጋር ደግሞ እህትህ ነች፡፡ እርሷ ለአንተ እናትም እህትም ነች፡፡ ከእነዚያ ከንጹሐን ደናግል ጋርም ሙሽራህ ነች፡፡ የእናትህ ውበቷ ሆይ፣ አንተ በሁሉ ነገር ከፍ ከፍ አድርገሃታል፡፡
3. እመቤታችን በአንተ ምክንያት ያገቡ ሴቶች ያሏቸውን ነገሮች ሁሉ ማለትም፤ ያለ ዘርአ ብእሲ ምጽነስን፣ ከተለመደው መንገድ ውጪ በጡቶቿ ወተትን፣ አግኝታለች፡፡ ደረቂቱ ምድር /Parched earth/ በድንገት የወተት ምንጭ አድርገሃታል፡፡
4. እናትህ እጅግ አስደናቂ ነች፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ መናገር የሚችል ሆኖ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ዝም አለ፤ የሁሉ እረኛ ሆኖ ገብቶ በእርሷ ውስጥ በግ ሆነ፤ እያለቀሰም ወጣ፡፡
5. የእናትህ ማኅፀን ሥርዓትን ሁሉ ሻረ፤ ሁሉን ያዘጋጀው /ሁሉ በእርሱ የሆነው/ ሀብታም ሆኖ ገባበት፤ ድሃ ሆኖም ወጣ፡፡ ከፍ ከፍ ያለ ሆኖም ገባና ትሁት ሆኖ ወጣ፡፡
6. ሃይለኛ ተዋጊ ሆኖ ገብቶ በእርሷ ማኅፀን ፍርሃትን ለበሰ፤ የሁሉ መጋቢ ሆኖ ገብቶ ረሃብን ተቀበለ፡፡ ለሁሉም መጠጥን የሚሰጥ ሆኖ ገብቶ ጥምን ተቀበለ፡፡ ለሁሉ ልብስን የሚሰጠው ከእርሷ ማኅፀን ራቁቱን ሆኖ ተወለደ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
|
No comments:
Post a Comment