Sunday, December 30, 2012

«ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን ለሰውም በጐ ፈቃድ»











«ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን ለሰውም በጐ ፈቃድ»
ዓለም በኃጢአት ጨለማ ተውጦ፣ ሰውና እግዚአብሔርም ተለያይተው፤ ሰላም ከሰው ልጆች መካከል ጠፍቶ በምትኩ ጥል፤ ክርክር፣ ምንዝር፣ ነፍስ መግደል አምልኮ ባዕድ ሌላውም ኃጢአት በዓለም ላይ ተስፋፍቶ፤ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያህል እንደኖረ  የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡
ነገር ግን ለዓለም ሰላም፣ የሚገኘው ከማን? በማን? እንደሆነ ነቢያት በየጊዜው እየተነሡ ይተነብዩ እንደነበር ከብሉይ ኪዳንና ከነቢያት መጻሕፍት አንብበን እንረዳለን፡፡ ይኸውም ለዓለም ሰላም፣ የሚገኘው ሁሉን ከሚችል ከእግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡ ሰላም በምድር፣ ለሰው ልጆችም በጎ ፈቃድ እንዲሆን እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ፡፡ ስለ እርሱም ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ «ኀያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» ሲል መስክሮለታል፡፡ ስለሆነም መድኅኒ ዓለም ክርስቶስ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ሲወለድ መላእክት ከሰማይ ወደ ምድር ከምድር ወደ ሰማይ እየተመላለሱ «ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ» እያሉ በዘመሩ ጊዜ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ እንደፈረሰ በምትኩም ሰላም፣ ዕርቅና ምሕረት በምድር ሁሉ ላይ እንደሰፈነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡
ክርስቶስ በቤተልሔም በሚወለድበት ጊዜ በመላእክትና በኖሎት አንደበት /ልሳን/ የሰላም አዋጅ እንደተነገረ ቅዱስ ወንጌል ጨምሮ ተርኮልናል /ሉቃ.2-10/
በዚሁ ዕለት ሰውና መላእክት ብቻ አመስግነው አልቀሩም፡፡ እንስሳት፣ አራዊት፣ የሰማይ አዕዋፍና የባሕር ዓሣት ሳይቀሩ ሰላም በምድር ተመሠረተልን እያሉ ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል፡፡ ምክንያቱም ሰላም በምድር ከሌለ ማንኛውም ፍጡር በሰላም በምድር መኖር አይችልምና ነው፡፡
መድኀን ክርስቶስ በዚህ በተቀደሰ ልደቱ የገለጸውን የቸርነት ምስጢርና በዙሪያቸው ያበራውን ብርሃን በቅርብ ሆነው ለማየት የታደሉ ዮሴፍና ሰሎሜ ናቸው፡፡ በመላእክት ተጠርተው የደስታው ተካፋዮች የሆኑትም በቤተልሔም ዙሪያ መንጋቸውን ተግተው ይጠብቁ የነበሩት የከብት እረኞች ናቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ይህን የሰላም ባለቤትና እውነተኛ ብርሃን ለማየት የታደሉ ሰብአሰገል የምሥራቅ ነገሥታት ለአምላክነቱ ለንጉሥነቱ የሚገባውን እጅ መንሻ ይዘው በኮከብ እየተመሩ ከቤተልሔም ደርሰው የልደቱ በዓል ተካፋዮች ሆነዋል፡፡ 
ክርስቶስ በልደቱና በጥምቀቱ የመሠረተውን ሰላምና ፍቅር እነሆ በዓለም የሚገኙት ክርስቲያኖች ልዩ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያከብሩታል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስተያን ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስክርሰቶስ ልደትና ጥምቀት ያላት አክብሮት  በጣም የተለየ ነው፡፡ በጾም በጸሎት ቆይታ በዓሉን በማኅሌትና በቅዳሴ አድምቃ ታከብረዋለች፡፡
በእርግጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትና ጥምቀት በክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ክብር የሚሰጠው ነው፡፡ ምክንያቱም በልደቱና በጥምቀቱም ከእግዚአብሔር በጸጋ ተወልደናልና፡፡ ከዲያብሎስም አገዛዝ ነፃ ወጥተናል ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋግረናል፡፡ ከፍርሃት ከሽብር ከጠብና ከክርክር ወጥተን ሰላምና ፍቅር አግኝተናል፡፡
አባቶቻችን ይህን የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ሰውና መላእክት አብረው አምላካቸውን በጋራ ያመሰግኑበት በወልድ ውሉድ የተባሉበትን ዕለት ቤተክርስቲያናቸው በሠራችላቸው ሥርዓት መሠረት ንስሐ ገብተው በጾም በጸሎት ተወስነው፤ በዐሉን ፀዐዳ ለብሰው በማኅሌቱና በጸሎተ ቅዳሴው ተሳትፈው ክቡር ደሙን ቅዱስ ሥጋውን ተቀብለው ያከብሩታል፡፡
በተጨማሪም ያላቸውን ለሌላቸው አካፍለው፣ የታረዙትን አልብሰው፣ የታሰሩትን  ጠይቀው የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን በግብር ይገልጻሉ፡፡ 

እኛም በወልድ ውሉድ የተሰኘን የክርስቶስ ቤተሰቦች በዐሉን የምናከብረው እንደ አባቶቻችን በንስሐ፣ በጾም በጸሎት እንጂ እንደ ዓለማውያኑ ታላቅ የሙዚቃ ዝግጅት በማዘጋጀትና በመታደም፣ ከልክም በላይ በመጠጣት በዋዛና በፈዛዛ አይደለም፡፡
ክርስቶስ ክርስቲያን የተባለው ክቡር ሰው በዓሉን ማክበር የሚገባው እንደ አባቶቹ በቤተክርስቲያን በመገኘት፣ ራሱን ለክቡር ደሙ ለቅዱስ ሥጋው ዝግጁ በማድረግ፣ ድሆችን በማሰብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ መሆን አለበት፡፡
ስለዚህ ይህን የጌታን ልደት ለማየት የታደሉ ዓይኖች የምሥራችን ለመስማት የበቁ ጆሮዎች ንዑዳን፣ ክቡራን ናቸው፡፡ አክብረን ለመክበር እንድንበቃ በዓሉን በደስታና ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ ሥርዓት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን ለሰውም በጎ ፈቃድ እያልን እምነታችንን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ 
ከላይ የገለጽናቸውን በጎ ምግባራት የምናከናውነው በዓል በመጣ ጊዜ ብቻ መሆን እንደሌለበትም ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የክርስቶስቤተሰቦች ሁሉ በጎ ምግባራት የየዕለት የሕይወታችን መመሪያዎች ሊሆኑ እንጂ በዓመት አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ ብቻ እያሰናቸው የሚያልፉን ሊሆኑ አይገባም፡፡ የበዓለ ልደቱ በረከትና
ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 






No comments:

Post a Comment