Tuesday, June 16, 2015

‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ››




‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ››
ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ ‹‹አኃዊነ ለኩላ መንፈስ ኢትአመኑ አላ አመክርዋ ለመንፈስ ለእመ እምኀበ እግዚአብሔር ይእቲ፣ ወንድሞች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ለእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ›› (1ዮሐ 4፡1) ይለናል፡፡
ሐዋርያው እንዲህ ባለ ምክር ልንጠነቀቀው የሚገባንን ነገር ያሳሰበበት ምክንያት ሐሰተኛ ነቢያትና መምህራን በሐሰተኛው መንፈስ እየተነዱ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በመታየታቸውና የሚያጠፋ ኑፋቄን በመዝራታቸው ነው፡፡ ይህንንም ሲገልጽ ‹‹ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና ይህን እንደመጣ ሰምታችኋል አሁንም እንኳ በዓለም አለ በማለት አክሎ ጽፎልናል፡፡ (1ዮሐ 4፡1-3)
እንዲሁም ርኩስ መንፈስ በየጊዜው የአሰራር ጥበቡን እየቀያየረ ትውልዱን ከምግባር እያራቆተ፣ ከኀይማኖት እያስወጣ ባህልና ቅርስ አልባ እያደረገ ነው፡፡
በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን በብዛት ከሚያስተዋሉትና ትውልዱን እያሰናከሉ ካሉት የርኩስ መንፈስ አሰራሮች መካከል መናፍቅነት፣ ደባል ሱስ፣ የሞራል ልሽቀት፣ ፍቅረንዋይና ሰዶማዊነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ትውልዱ የሩቅ ናፋቂ ከመሆኑ የተነሣ የራሱን ባህልና ቅርስ አክብሮ በኦርቶዶክሳዊነት ውብና ድንቅ ትውፊቶች ከማጌጥ ይልቅ የምዕራቡ ዓለም የሴኬም አሸንክታብ አጉልና ጎጂ ባህሎች ማራገፊያ ወደብ በመሆኑ ለክፉው መንፈስ መሣሪያነት ራሱን አጋልጦ እየሰጠ ነው፡፡
ርኩስ መንፈስ አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን የመጣ ሳይሆን ከአባታችን ከአዳም ጀምሮ የሰውን ዘር ሁሉ ከእግዚአብሔር ለመለያየት ሲፈታተን የቆየ የነቢያት የሐዋርያትን ትምህርት ከምዕመን ዘንድ እንዳይደርስ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ በፈሪሳውያንና በመሰሎቻቸው እያደረ ምንፍቅናን ክህደትን ይዘራ ነበር፡፡ (ማቴ 12፡14 ፣ ማቴ 16፡6፣ ማር 2፡16)
ሐዋርያው ጳውሎስ እስራትና መከራ እደሚያገኘው መንፈስ ቅዱስ ካመለከተው በኋላ በዘመኑ በኤፌሶን ለነበሩ ጳጳሳትና ቀሳውስት እንዲህ ብሏቸዋል ‹‹አሁንም እንሆ እኔ የእግዚአብሔርን መንግስት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችን ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳታዩ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ አውቃለሁ›› (ሐዋ 20፡25-33)
በመሆኑም ሐዋርያው እንደተናገረው እስከፍጻሜ ዓለም ርኩስ መንፈስ የምእመናንን ሕይወት በመፈታተንና በቅድስት ኃይማኖታቸውም ጥርጥርን ለመዝራት ብዙ ታግሏል፣ ይታገላልም፡፡ ምንም እንኳ ርኩስ መንፈስ በተቀደሰች ጉባዔ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ ጥርጥርን፣ መለያየትን ለመዝራት ጦሩን ሰብቆ ቢወረውረውም ቤተክርስቲያንን ሊጣናውጻት አልተቻለውም፡፡ (ማቴ 16፡18)
በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖችንም ርኩስ መንፈስ በልዩ ልዩ መልክ መፈታተኑ አልቀረም፡፡ በልዩ ልዩ ስልት ወይም ዘዴ ከመንፈስ ቅዱስ በሚመስል አሰራር በአንዲት ንጽሕት ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸንተን እንዳንኖር ይፈታተነናል፡፡ በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ምልክት እናሳያለን የሚሉ ነቢያተ ሐሰት እንዲሁም መናፍቃንን እያስነሳ ዘወትር ትውልዱን ይፈታተናል፡፡
እውነተኛ ክርስቲያን እንደ ቅድስት አፎሚያ ቅዱሳን መላዕክትን ከርኩሳን አጋንንት መለየት ይኖርበታል፡፡ ዲያብሎስ ከቅድስቲቱ ዘንድ ቀርቦ ‹‹በየወሩ በስሜ ለነዲያን የምትዘክሪልኝ ጠባቂሽ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ›› ቢላት በንግግሩ ተደንቃ አልተቀበለችውም ፡፡ ይልቁኑ ከቅዱሳን መላዕክት ዘንድ የማይለየው ተእምርተ መስቀልን አለመያዙ በእርግጥ እርሱ ፀረ-መስቀል መሆኑን አወቀችበት እንጂ (ድርሳነ ሚካኤል-ዘሰኔ)
አበው በምሳሌ ‹‹ጠርጥር ገንፎ ውስጥም አለ ስንጥር›› እንዲሉ የእውነት መንፈስና የስህተት መንፈስን ለይተን የምናውቅበት መለያ ሊኖረን ይገባል፡፡
ዓለም በውበቷና በብልጭልጭነቷ የምታታልለው አንሶ ሐሰቱን እንደ እውነት መራራውን እንደጣፋጭ፣ ክፋቱን እንደ መልካም ነገር፣ ኀጢዓቱን እንደጽድቅ እየሰበከች ትውልዱን ወደ ሞት እየነዳችው ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ክፉ መንፈስ መቋቋም የሚቻለው በፍጹም ኀይማኖት በመጽናት፣ በትክክለኛው ጎዳና በመጓዝ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በተመሠረተችው በነቢያትና በሐዋርያት በተሰበከችው በሰማዕታት ደም በጸናችው ለቅዱሳን ፈጽሞ አንድ ጊዜ በተሰጠችው በኦርቶዲክስ ተዋሕዶ የእምነት ጥላ ሥራ በመሰባሰብ ነው፡፡ (ይሁ 1፡3 ፣ ዕብ 3፡14)
ሐዋርያው ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው›› ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በተዋሕዶ የከበረ ሆኖ የተገለጠ መሆኑን የሚታመን መንፈስ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይልቁንስ የክርስቶስ ተቋዋሚ መንፈስ ነው እንጂ፡፡ (1ዮሐ 4፡2-6) ስለዚህም ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት ሳይወሰዱ በብልጭልጩና ኃላፊ ጠፊ በሆነው ዓለምም ሳይታለሉ መንፈስን ሁሉ እየመረመሩ ኀይማኖትን አጽንቶ ምግባርን አቅንቶ መኖር የዘመኑ ሰማዕትነት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment