Friday, April 24, 2015

ሰማዕትም ሆኑ ማዕተብን አስረው






በዚህ ሳምንት እንኳን
እባካችሁ ተውን
የኢትዮጵያዊነት ክብራችን ተነክቶ
የሥላሴ ህንፃ ፈርሶ ተንኮታክቶ
እምነት በሌላቸው በአህዛብ ተዋርደን
ተንቀናልና መሳለቂያ ሆነን

      እባካችሁ ተውን እናፍስ እንባችን
      አልቅሰን ይውጣልን መከራ ሲቃችን
      እንዘን እንተክዝ ለወገኖቻችን
      አለምም ይመልከት ይህንን ግፋችን
      በአደባባይ ወጥተን እንባ ማፍሰሳችን
እህት ወንድሞቹን ሁሉንም ሰው ሊያደርግ
ምስኪኗን እናቱን ከረሃብ ሊታደግ
ጥቂት ስንቅ ሊያመጣ ከቤት እንደወጣ
በዚያው ቀርቷልና ከቀየው ሳይመጣ

      እባካችሁ ተውን እርማችንን እናውጣ
      በሊብያ ሜዳ በጥይት ተቆልተው
      በባህር ዳርቻ እንደ በግም ታርደው
      ሰማዕታት ለሆኑት በክርስትናቸው
      እባካችሁ ተውን እርማችን እናውጣ
      የሚያሰጡንንም በረከት አንጣ
      ድንገት ይኖር ይሆን የሚፈርድባቸው
ከቀየ ከመንደር ከሀገር ስለወጡ
እንጀራን ለመጥገብ እጅ ስለሰጡ
ኢትዮጵያዊነትን ጠልተውት አይደለም
ያደጉበትን ወግ ንቀውም አይሆንም
ወገናቸውንም አቃለው አይደለም
ቢቸግራቸው ነው ማጣፊያው ሲያጥራቸው
ደሀ ተበድሎ ፍርድ ቢጓደል ነው
አስተዋይ ሰው ጠፍቶ ከኢትዮጵያ ምድር
ሁሉን አንድ አድርጎ አፍቅሮ የሚያፋቅር
መንጋውንም መርቶ ህዝቡን የሚያሻግር
እግዚአብሔርን ፈርቶ ሰውን የሚያከብር
      ከቤትም ሲወጡ ተስፋውን ሰንቀው
      ልክ የዛሬ ዓመት እንመጣለን ብለው
      መስዋዕት አቅርበው ስዕለትን ተስለው
      ሀገር ለመመለስ ነበረ ቃል ገብተው
አሁን አስከበሩን በእምነታቸው ፀንተው
ሰማዕትም ሆኑ ማዕተብን አስረው
የቅዱስ ጊዮርጊስን ፋና ተከትለው
      ምንም እንኳን ብናዝን በሰብአዊነት
      ሙሾ ብናወጣ ብንደቃ ደረት
      ግን ተደስተናል በሰሩት ጀግንነት





No comments:

Post a Comment