Friday, April 24, 2015

አስብ የሆነብን





ጊዜ የሰጠው ቅል ዓለቱን ሠበረ
የዓለቱን ልጆች እጅና እግር አሰረ
ርስታችን ሁሉ ገብቶ መዘበረ
ኀያላንን ገድሎ በይፋ ፎከረ
      እንጀራ እንጠግብ ዘንድ
      ብንሰጥ እጃችን
      ባሪያዎች አረጉን በገዛ ብራችን
      የገዛ ውኀችን በብራችን ጠጣን
      እንጨታችንንም በዋጋ ሸጡልን
የተናቀ አሕዛብ ማተብ የሌላቸው
በሚዛን ላይ ያሉ ጥቃቅን ትቢያዎች
በገንቦ ውስጥ ያሉ ጥቂት ጠብታዎች
      ኑሮን ልናቀና ብንመጣ ሀገራቸው
      ቅርጫት ተሸክመን ብንሄድ ቀያቸው
      ባሪያዎች አይለው ከለዳውያን ገነው
      ደመ ከልብ አረጉን ደማችን አፍሰው
ከምድረ በዳ ሰይፍ ሐሩር የተነሳ
ቁርበታችን ጠቁሮ መልካችን ተረሳ
ኢትዮጵያዊ እንደሆን ጠላትም ረሳ
ደማችንን ሊያፈስ ብረቱን አነሳ

      በገዛ ምድራችን በአህጉራችን
      በአደባባይ ተጣልን በእሳት ተቃጠልን
      በባህር ዳርቻ እንደ በጎች ታረድን
      በግፍ ተደበደብን በጥይት ተገደልን
ክብራችንን ጥለን ስደት ብንወጣ
ሕይወታችን ሸጠን ንዋይ ልናመጣ
ወገን እንደሌለው ተዘባበቱብን
መሳለቂ አድርገው አፍም ከፈቱብን
ሀገር እንደሌለው ባይተዋር አረጉን
      አሁን ግን አቤቱ አስብ የሆነብን
      ልባችን ታመመ አይናችን ፈዘዘ
      ንቀትንም ጠገብን እጅግም ተዋረድን
      በየአደባባዩ መጠቋቀሚያ ሆን
      እባክህ ፈጣሪ ወደ አንተ መልሰን
      እኛም በንስሐ እንመለሳለን
      ቀሪ ዘመናችን እንደቀደሞው አድስ
      ስድባችንንም እይ እንባችንም አብስ
      ዳግም ተመልሰን እንበል ቅዱስ ቅዱስ
      አንተ ነህ ታዳጊ ለሁሉ የምትደርስ

     

No comments:

Post a Comment