Sunday, October 21, 2012

“ወኢንህድግለነ ማህበረነ”መሰባሰባችንን አንተዉ (ዕብ 10፡25)




ከፍረት አለም ጀምሮ ቅዱሳን መላእክት ሆኑ የሰዉ ልጆቸ እግዚአብሄርን በህብረት  ሆነዉ እንደየተፈትሮአቸዉ እንደሚያመልኩት መፅሃፍት ያስረዱናል ፡፡በብሉይ  ኪዳን አይሁድ ለእግዚአብሄር በለዩት ስፍራ በማህበር በመሰባሰብ እግዚአብሄርን ያመልኩት ነበር፡ ለስሙም መስዋእትን በፊቱ ያቀርቡ ነበር ፡ ፡በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ  በመሆን በህብረት ይጸልዩና በሰሙ ይሰበሰቡ እንደነበር ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ስራ ላይ ዘግቦት እናነባልን፡፡ ሐዋ4፡32   ይህን ማህበርም  ለእዉነተኖች ክርስቲያኖች አስረክበዉ አልፈዋል፡ ፡

ከዚያም በሀዋላ የተነሱ እዉነተኖች ክርስቲያኖች በወንጌል “አንድም ወይም ሁለትም ሆናችሁ በስሜ ብትሰበሰቡ እኔ በመካከላችሁ እገናለሁ የሚለዉን ቃል መሰረት በማድረግ በዘመናቸዉ ይነሱ የነበሩ ፈተናዎችን ሁሉ ታግሰዉ በ እግዚአብሄር ስም ባንድ ልብ በማህበር በጉባኤ ይሰባሰቡ ነበር፤ አንድነታቸዉን ና የመንፈስ  ህብረታቸዉን አልተዉም ፡፡ በመንፈስ አንድ መሆን ሀይል ነዉ ጠላትን ድል ያደርጋል፡ ዳሩ አበዉ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ይሉ የለ፡፡ስለ ጽድቅ ብለዉ በህብረት የሚቆሙ ጸሎታቸዉ ከቅድመ እግዚአብሄር ይደርሳል፡፡በህብረት ና በ አንድነት የሚቆሙ ሁሉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን በሀይማኖት ጎዳና ያበረታሉ፡፡ ታዲያ ቅዱስ ጳዉሎስም መሰባሰባችን አንተዉ በማለት ለዕብራዉያን ሰዎች የጻፈዉ ይህ ሲዎርድ ሲዋረድ ለዘመናት በምእመናን ዘንድ የነበረዉ የ አንድነትና የመሰባሰብ መንፈስ እንዳይናጋ ለማሳሰብ ነዉ፡፡ ምክንያቱም በጊዚያት ሁሉ ና በየዘመኑ ሰዎች ለእግዚአብሄር በሐይማኖት ተለይተዉ በ አንድ ሃሳብ መሰባሰባቸዉን የማይዎድ ጠላታቺን ዲያብሎስ የመለያየትን ዘር ከመዚራት ስለማይመለስ ነዉ፡፡
መሰባሰባችን አንተዉ የሚለዉ  የእግዚአብሄር ቃል በተለይ በዚህ በመጨረሻዉ ዘመን ላለነዉ ክርስቲያኖች በአጽንኦት ሊነገር የሚገባ ነዉ፡፡ ዘመኑን በመዋጀት በየወቅቱ የሚነሱብንን ልዩ ልዩ ፈተናዎች የ እግዚአብሄርን ቃል ጋሻ አድርገን በጥበብ በመመላለስ በትእግስት ልናሳልፋቸዉ ይገባል እንጂ በየምክንያቱ መለያየት አያስፈልግም፡፡ወገንተኝነትን ዘረኝነትን ትተን ሁላችን በክርስቶስ አንድ መሆናችን አስበን በፍቅር እንቁም፡ ፡ከዉስጥም ሆነ ከዉጭ ለሚመጡት መከራዎችና ፈተናዎች ለምናያቸዉ ችግሮች አንዳችን በ አንዳችን ላይ ጣታችን ከመቀሰር ይልቅ የራሳችን ድክመት እያረምን አንድነታችን እናጠናክር፡፡ አንዱ ሌላዉን ጠልፎ  የሚጥልበትን የ እንቅፋት ድንጋይ ከማዘጋጀት ፡ጉድጋድ ከመቆፈር ታቅበን አንድ የሚያደርገንን ሃሳብ መያዝ ለትዉልዳችን አማራጭ የሌለዉ መንገድ ነዉ፡፡ በክርስቶስ በኩል ያገኘነዉን የአንድነት ፀጋ ጥለን ብንያይ ግን ሐዋርያዉ እንዳለ መጠፋፋት እንጂ ለቤተክርስቲያን ትርፍ አይሆናትም፡፡”እርስ በ እርሳችሁ ብትነካከሱ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ”” ገላ5-15
በተለያዩ ማሕበራትም  የመሰባሰባችን አላማዉ አንዱ አንዱን ለማነፅና ለማበርታት ለፍቅርና ለመተያየት ሊሆን ይገባል፡፡መሰባሰባችን ለበጎ አላማ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት እንጂ ጌታን በሃሰት ከሰዉት ለመስቀል ተሰብስበዉ እንደመከሩ አይሁድ ሌሎችን ለመቃዎመና ለመበተን አይሁን፡፡ ይህ ለቤተክርስቲያን ድል አይደለምና፡፡በእዉነት የቤተከርስቲያናችን ትንሳኤ ለማየት የምንሻ ሁሉ ከመቃቃር መፋቀርን ከመናናቅ መከባበርን ከመተቻቸት መተራረምን ከመለያየት መስማማትን ከመገፋፋት መቀራረብን ልንመርጥ ይገባል፡፡
እንግዲህ አባቶቻችን ሐዋርያት እንደ አንድ ልብ ይመክራሉ እንደ አንድ ቃል ይናገራሉ ስንል በጊዜአቸዉና በዘመናቸዉ የተከሰቱትን ችግሮች በማስተዋልና በጥበብ በፍቅር ሆነዉ እየተመካከሩ በመፍታት የጠፋዉን እየፈለጉ የደከመዉን እያበረቱ በፆምና በፀሎት ተግተዉ ለዛሬዎቹ ምዕመናን ይችን እምነት ስላወረሱን ነዉ፡፡ እኛም በመንጋዉ ሞልታ የተረከብናትን የሐዋርያት ማህበር ቤተክርስቲያንን ሳትበተን ለሚቀጥለዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ እኔነትንና እልከኝነትን አዉጥተን ፍቅርን አጥብቀን እንያዝ፡፡ቀድሞ በነቢያት በሃላም በሐዋርያትና በሊቃዉንት ከዚያም በሀላ እንደተነሱት የ እግዚአብሄር ምርጦች ለመልካም ስራ ለመነቃቃት ለፍቅር ብቻ የመቆምን መንፈስ አጽንተን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ መጽሐፍ  “ከበጎ ጋር ተባበሩ…” እንዲል በጎ ህሊናና ሀሳብ ከላቸዉ በሃይማኖት ከሚመስሉን ሁሉ ጋር በመንፈስ መሰባሰብ መልካም ነዉ፡፡ይልቁንስ ስለቤተክርስቲያን አንድነት መመለስና መጠበቅ ስንል ይህን አጥብቀን እናድርግ ለዚሁም እግዚአብሄር ይርዳን፡፡




1 comment:

  1. “ከበጎ ጋር ተባበሩ…” እንዲል በጎ ህሊናና ሀሳብ ከላቸዉ በሃይማኖት ከሚመስሉን ሁሉ ጋር በመንፈስ መሰባሰብ መልካም ነዉ፡፡ይልቁንስ ስለቤተክርስቲያን አንድነት መመለስና መጠበቅ ስንል ይህን አጥብቀን እናድርግ ለዚሁም እግዚአብሄር ይርዳን፡፡

    እውነት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete