Sunday, October 28, 2012

ተዋሕዶ መጠርጠር የሌለባት ሃይማኖት








ካለፈዉ የቀጠለ….

እናም ትንቢቶቹ በመሀመድ ወይም በሉተር አልያም ከእነርሱ ወዲህ ለተመሰረተ ሃይማኖት የተነገሩ ናቸዉ ተብሎ እንኳን ቢታሰብ ፍጹም የማይመስል ነገር ነዉ፡፡ምክንያቱም መስራቾቹ እነርሱ እስከሆኑ ድረስ ከመሀመድ ወይም ከሉተር በፊት ሃይማኖት አልነበረም እንዴ ? ተብሎ ቢጠየቅ መልስ አይኖርም፤ምናልባት ላለማመን ተብሎ ሌላ ነገር ካልተነገረ በቀር ማለት ነዉ ወይም በሌላ በኩል ከእነ መሀመድ እና ሉተር በፊት የነበሩ ሐዋያት ቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት በሙሉ እነ ሉተር ዘመን ላይ ስላልደረሱ እነዚህ ሁሉ ሃይማኖት አልነበራቸዉም ማለት ነዉ? ሰዉነታቸዉ እንደ ሽንኩርት በሰይፍ የተቀረደደዉ ፤ በእሳት የተቃጠለዉ ፤ አጥንታቸዉ  እየተፈጨ በንፋስ የተበተነዉ ፤ ቆዳቸዉ ተገፎ አቅማዳ እስኪሆን ድረስ ያደረሳቸዉና ያን ሁሉ ሰማእትነት ይከፍሉ የነበረዉ ገና ወደፊት ፍር ለሚመሰርተዉ ሃይማኖት ነበር ማለት ነዉ?






በጭራሽ እረ እነርሱስ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠችዉ ለቀደመችዉ መንገድ አንዲት ብቻ ለሆነችዉ ለተዋህዶ ሃይማኖታቸዉ ለአምላካቸዉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ነዉ ያን ሁሉ ሰማእትነት ሲቀበሉ የነበረዉ፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ወልድ ዋሕድ ሁለት ልደት ብሎ በመሰከረ ጊዜ በእርሱ አለትነት ለተመሰረተችዉ ቤተክርስቲያን ሲሉ ነዉ ያን ሁሉ መከራ የተቀበሉት እንጂ ከተመሰረተዉ መሰረት ዉጪ ሌላ መሰረት እንደማይመሰረት ያዉቁታል፡፡ማቴ16፡18  እንዲሁም “ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ታንጻችሀዋል”ፊሊ2፤20 “ከተመሰረተዉ በቀር ማንም ሌላ መሰረት ሊመሰርት አይችልምና እርሱም ክርስቶስ ነዉ”1ኛ ቆሮ3፤11  ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ነዉ እስከሞት ድረስ ታምነዉ  የሕይዎትን አክሊል የተቀዳጁት።
እነርሱ በዚህ መልኩ ያጸኗትን ሃይማኖት ነዉ ለተረካቢዉ ትዉልድ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ለተጠራን ለእኛ ያስረከቡን፡፡ የእነርሱን  ሃይማኖት እስካልተከተልን ድረስ ክርስቲያን ነኝ ማለት አይቻልም፡፡እናም ሐዋርያቱ ወልድ ዋሕድ  ብለዉ ያጸኗትን ሃይማኖት የእነ ቅዱስ አትናቴዎስን ፤የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን፤ የእነቅዱስ ዮሐንስ አፈዎርቅን ፤ የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን …….ሃይማኖት ያልተከተል ለአፉ ካልሆነ በቀር ክርስቲያን ነኝ ማለት አይችልም፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ  “ የመጀመሪያ እምነታችን እስከመጨረሻዉ አጽንተን  ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናል “  ዕብ3፤4 በማለት  ከማሳሰቡ ባሻገር አሁንም በክርስቶስ ክርስቲያን ለመሰኘት እነዚህ የቀደሙ አባቶቻችን የነገሩንን እንድናስብ  በሃይማኖትም እንድንመስላቸዉ  አዟል  “ የእግዚአብሔርን  ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸዉንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖት ምሰሉአቸዉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትላንትና ዛሬ እስክ ዘላለም ያዉ ነዉ፡፡ ዕብ13፤7 እናም ዛሬ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳዉሎስን ትዕዛዙን ፈጽመንለት እርሱ ያሰተላለፈላቸዉን የአባቶቻችንን ሃይማኖት ተከትለን በእምነት መስለናቸዉ ብንገኝ ደግሞ በጣም ይደሰትብናል፡፡ ስለዚህም ነዉ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቲዎስ “ በእናትህ በኤዎንቄ ፤ በአያትህም በሎይድ ጸንታ ያለች መጠርጠር የሌለባትን ሃይማኖትህን አይቼ ደስ አለኝ ፡፡ባንተ ጸንታ እንዳለች አምኘ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡” 2ኛ ጢሞ1፤5 በማለት የጻፈለት፡፡ታዲያ እኛስ እናትና አባቶቻችን ያጸኗትን ሃይማኖት አጽንተን ይሆን? መጠርጠር የሌለባትን ሃይማኖትህን አይቼ ደስ አለኝ ፤ እዉነትም ቅድስትና ጥርጥር የሌለባት  አንዲት ሃይማኖት፡፡
ከሊቢያ የተወለደዉ አርዮስ “”ወልድ ፍጡር ነዉ”” በማለቱ በ325ዓ.ም 318ቱ ጳጳሳት አባቶች በኒቂያ ተሰብስበዉ ለዩትና ከቅዱሳን ሓዋርያት በአደራ የተረከባትን አንዲት ሃይማኖት ኦርቶዶክስ የሚል ስያሜ ሰጡት፡፡ቀጥተኛ መንገድ ማለት ነዉ ፡፡እንደገና ከግሪኮች ዘር በሮም የተወለደዉ መቅዶኒዮስ ”እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል “ብሎ በሐሰት በመነሳቱ በ381ዓ.ም 150 ቅዱሳን አባቶች በ ቁስጥንጥንያ ተሰብስበዉ አወገዙት፡፡ሊቃዉንቱም አምላክ ሰዉ ፤ ሰዉ አምላክ ሆነዋል ሥጋና መለኮት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋል ሲሉ ኦርቶዶክስ በሚለዉ ስያሜ ላይ “ተዋሕዶ” የሚል ስያሜ ጨመሩለት፡፡ እንደዚሁም ከሮማዉያን ዘር የተወለደዉ  ንስጥሮስ “” እግዚአብሔር ወልድ ሁለት አካል ሁለት ባሕሪይ ነዉ ፤ ድንግል ወላዲተ አምላክ አትባልም “ በማለቱ በ431ዓ.ም 200 ቅዱሳን አባቶች በ ኤፌሶን ተሰብስበዉ አወገዙት፡፡ “እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካልን ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይን ገንዘብ ያደረገ አምላክ ነዉ፤ቅድስት እናቱም ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት” በማለት ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አጸኗት፡፡ ከ 451ዓ.ም በሀላ ግን ሁለት ባሕርይ ባዮች ተገንጥለዉ ምዕራባዊ ፡ካቶሊካዊ እምነትን አቐቐሙ፡፡
በመሆኑም ቅድስት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ በጌታችን ደም የተመሰረተችዉ በ 12ቱ ሐዋርያትና በ72ቱ አርድዕት በአለም ላይ የተስፋፋች  በ318፤ በ150፤እና በ200 ቅዱሳን አባቶች የጸናች በቅዱሳን ጻድቃን ጽኑ ተጋድሎ ና            በሰማእታት ደም ያሸበረቀች ናት፡፡በመሆኑም መጠርጠር የሌለባት ሃይማኖት ማለት   ይህቺ ናት ቅድስት ተዋሕዶ፡፡



No comments:

Post a Comment