Thursday, November 1, 2012

“የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር”




“የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር”
(ብፁእ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቃየ ፤ ነገር ግን ስለእኛ ተሰቃየ ፡ ስለእኛ ተሰቃየ ፤ እኛን ከስቃይ ከህማም ያድነን ዘንድ እርሱ ተሰቃየ ፡ እኛን ከሞት ያድነን ዘንድ ሞተ ፤ እኛን ከድካም ያሳርፍ ዘንድ እርሱ በእጅጉ ደከመ ፤ ክርስቶስ እኛን ያድነን ዘንድ ተሰቃየ ፡ ስለሌሎች ተሰቃየ ፤ ህማሙ በነፍሱና በስጋው ላይ ወደቀ ፡ ለረጅም ሰአት መስቀሉን ተሽክሞ ነበርና ፡ በሚወድቅ ሰአት ከባዱ መስቀል ተጭኖት ነበርና ፡ የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተው እንዲንገላታ አድርገውት ነበርና ፡ ቅዱስ ስጋውን በሚስማር ቸንክረው እንዲሰቃይ አድርገውት ነበርና ፡ በመስቀል ላይ ለረጅም ሰአት ተሰቅሎ ነበርና ፡ ደሙ እንደውሃ ፈሶ ነበርና ፡ ተደብድቦ ተገርፎም ነበርና ፤...
ደበደቡት ፡ ገረፉት ፡ ተፉበት እኒህ ሁሉ የጌታችን የስጋ ህማሙ ናቸው ፤ ነገር ግን የተቀበለው መከራ ይህ ብቻ አይደለም ፤ የስጋ ህማም ያልሆነ የነፍስ ህማምንም ታግሷል እንጂ ፤ እንደ ርጉም እንደበደለኛ መቆጠሩ ይህ አንዱ ህማሙ ነበር ፡ የመሰደቡ ህማም ይህ አንዱ ህማሙ ነበር ፡ በሁሉ ፊት መዋረዱ ይህ አንዱ ህማሙ ነበር ፡ የመካድ ህማም ፡ በሁሉ የመወገዝ ህማም ፡ እኒህም ሌላው ህማሙ ናቸው ፤ ሃዋርያቱ እንኳን ሳይቀሩ ትተውት ሽሹ ፡ ጴጥሮስ እንኳን ሶስት ጊዜ ካደው ፡ በወንድሞች መካከል በድካም መታየት ይህ ራሱ ለነፍስ ትልቅ ህማሟ ነው፡፡
ጌታችን ግን ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስበት ራሱን ይከላከል ዘንድ ምንም አላደረገም ፡ ራሱን አልተከላከለም ፤ በገዥወች የፍርድ ዙፋን ፊት በቆመ ጊዜ የውሽት ምስክሮችንና ክሶችን አቀረቡበት ፡ እርሱ ግን ዝም አለ ፡ ምላሽም አላቀረበም ፡ “አንተ ስለራስህ አትናገርምን? እኒህ ሁሉ ባንተ ላይ ሲመሰክሩ እንደምን ዝም ትላለህ?” እስኪሉት ድረስ ዝም አለ ፡ በጲላጦስም ፊት ሁሉ በሃሰት ሲከሱት ምንም አልተናገረም ፡ ዝም አለ እንጂ ፤ ራሱን ይከላከል ዘንድ አንዳች አላደረገም ፤ ራሱንስ ይከላከል ዘንድ ቢወድ ይህ በእርሱ ዘንድ እጅግ ቀላል ነበረ ፡ በክርስቶስ ዘንድ ያለ እውቀት ፡ ማመዛዘን ፡ መረዳትና ማሳመኛ ሊከላከልለት በቂ ነበርና ፤ ነገር ግን ፈቃዱ ራሱን ይከላከል ዘንድ አልነበረም ፡ ፈቃዱ ሌሎች ያድን ዘንድ ነበር እንጂ ፤ ሌሎቹም ይድኑ ዘንድ እርሱ መሰቀል ነበረበት ፤ ታገሉት “ አንተ የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ ራስህን ከመስቀል ላይ አውርድ” እያሉ ታገሉት ፤ እርሱ ከመስቀል ወርዶስ ቢሆን እኛ ሁላችን በጠፋን ነበር ፤ እርሱ ግን እኛ እንድንለት ዘንድ ስለእኛ በእነሱ መሽነፍን ወደደ ፡ ስላቃቸውን ይታገስ ዘንድ መረጠ ፤ እራሱንስ ይከላከል ዘንድ አልወደደም ስለሁሉ ሰው መከላከልን መርጧልና ፡ እኛን ያድን ዘንድ ስለሁሉ እርሱ ዋስ ሆነ ፤

ዳግምም ጌታችን ራሱ ስለራሱ ፈቃድ ተሰቃየ ፤ ራሱ ? እንደምን በራሱ ፈቃድ ተሰቃየ? ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ክርስቶስ ራሱ አይሁድ ሊይዙት ወደሚፈልጉበት ቦታ በእግሩ ሄዷልና ነው ፡ የት ቦታ አይሁድ ሊይዙት እንደተማከሩ እርሱ አስቀድሞ ያውቅ ነበርና ፡ ጊዜውንም ያውቅ ነበርና ፡ ስለዚህም እርሱ ራሱ ወደሚይዙበት ቦታ ሄደ ፡ ይሁዳ አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ራሱን አሳልፎ ሰጠ ፡ ዳግምም በራሱ ፈቃድ ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ ፡ ስለዚህም እንደዚህ አለ ፦ “ነፍሴን ላጠፋትም ላነሳትም ስልጣን አለኝ” በዚህም ከሚደርስበት ስቃይ ሁሉ ራሱን ይጠብቅ ዘንድ ይችል ነበር ፡ ነገር ግን በጄ አላለም ፤ እርሱ በራሱ ፈቃድ ለእኛ ራሱን መስዋእት አደረገ፡፡
በጌታችን በክርስቶስ ያየነው ስቃይ ሁሉ ጌታችን ለእኛ ያለው የፍቅር ምልክቶች ናቸው ፤ ጌታችን “ስለወዳጆቹ ነፍሱን ከሚሰጥ የሚበልጥ ፍቅር የለም” አለን ፡ ስለዚህም እነዚያ ስቃዮቹ ሁሉ ስቃዮች ብቻ አልነበሩም ፍቅሩም ነበሩ እንጂ ፤ እንግዲህ እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለውን ፍቅር ያሳይ ዘንድ ሃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለእኛ ሞተ ፤ የክርስቶስ ስቃይና ፍቅሩ የሚለያዩ አይደሉም ፤ የክርስቶስ መስዋእት የፍቅር መስዋእት ነው ፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ያመነ ሁሉ እንዲድን እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ አለሙን ወዷልና ፤ ስለዚህ ክርስቶስ ስለእኛ ባለው ፍቅር ስቃይን ተቀበለ ፤ በእኛ ላይ ባለው ፍቅር ምክንያት ባይሆን ኖሮማ ስለእኛ ባልሞተ ነበር ፤ እንግዲህ እኛም ክርስቶስን መልሰን እንውደደው ፡ ስለወደደን እንውደደው ፤ የክርስቶስ መከራ ራሱን ባዶ በማድረግ የተገለፀ ነበር ፤ እንዴት? ምናልባት አንዳንዶቻችሁ ክርስቶስ የሰውን ስጋ በለበሰ ጊዜ ራሱን ባዶ አድረገ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል ፡ ልክ ናችሁ ፤ እርሱ የባርያን መልክ መያዙ ፡ በሰው አምሳል መገለጡ ፡ በከብቶች በረት መወለዱ ፡ ይህ ሁሉ ራሱን ባዶ ማድረጉ ነው፡፡
ነገር ግን የሚበልጠው ራስን ባዶ ማድረግ በስቅለቱ የፈፀመው ነው ፤ ምክንያቱም ጌታችን ሃይሉን ይጠቀም ዘንድ ይችል ነበርና ፡ ነገር ግን ሃይሉን ይጠቀም ዘንድ አልወደደም ፡ ሊያስሩት በመጡ ጊዜ ሃይሉን አልተጠቀመም ፡ በፍርድ ወቅትም ሃይሉን አላሳየም ፡ በስቅለቱ ጊዜም ሃይሉን አላሳየም ፡ በጥፊ በመቱት ጊዜ ፡ በውርደት ፊቱ ላይም በተፉበት ጊዜ ሃይሉን አልተጠቀመም ፤ ሃይሉን አልተጠቀመም ፡ እርሱ ራሱን ባዶ አድርጓልና ፤ ራስን ባዶ ማድረግ!! ሃይሉን አልተጠቀመም ፡ ነገር ግን ይቅርታውን ተጠቀመ ፡ ስለዚህም በቅዳሴአችን “አንተ የክፉወችን ማስጨነቅ ታግሰሃል” እንላለን ፡ “መታገስ - ምን? የክፉወችን ማስጨነቅ ፡ ጌታ ሆይ “ ከሃፍረትና ከምራቅ መተፋት አንተ ፊትህን አላዞርክም ፡ ከአይሁድ ጥፊም ጉንጮችህን አላራቅክም” ፤ ይችል ነበር ነገር ግን ለእኛ ሲል ከእንግልት ራሱን አላረቀም ፡ በእኛ ላይ ስላለው ፍቅር የተነሳ ከመከራ አልሽሽም፡፡ የማዳን ስራውን ይጨርስ ዘንድ እስከመጨረሻው ታገሰ ፡ ይህ ነው እንግዲህ የሚበልጠው ራስን ባዶ ማድረግ ፤ ራስን ባዶ ማድረግ፡፡
የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር እጅግ በሃይል የተሞላ ነበር ፡ ይህ ሃያል ፍቅሩ በፅናቱ ብቻ የሚገለፅ አይደለም ፡ በማዳን ስራውም ጭምር እንጂ ፤ ክርስቶስ በጥልቅ ፍቅሩ ፡ በመታሰሩ ፡ በሞቱ የዲያቢሎስን ራስ ቀጠቀጠው ፡ የዲያቢሎስን ራስ ቀጠቀጠው !! የደረሱበትን ስቃዮችና ውርደቶች ሁሉ በትእግስት በመቋቋሙ ሃይለኛ ነበር ፤ በዝምታው ውስጥ ስለራሱም ባለመከራከር ውስጥ ሃይለኛ ነበር ፡ እርሱ ሃይለኛ ነበር ፡ በሞቱ ሞትን አሽንፎታልና ፤ እርሱ ሃይለኛ ነበር ዲያቢሎስን ድል ነስቶታልና ፤ እመኑኝ ስለክርስቶስ ከሚነገሩት የተመረጡ ንግግሮች ሁሉ በጣም ግሩሙ “ራሱን ባዶ አደረገ” የሚለው ነው ፤ ስለመዳናችን እንዲህ ተነገረ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤” ከዚህ የሚበልጥ ራስን ባዶ ማድረግ አለን? እርሱ ስለእኛ መተላለፍ እንደተቀሰፈ ተቆጥሯልና ፤ ግር የሚለው ነገር ህግ ተላላፊወች ሁሉ በግራ የተሰቀለው ወንበዴ እንኳን ሳይቀር በአንደበታቸው በውርደት ቃል እየሰደቡት የነበረ መሆኑ ነው ፡ በቀኝ የነበረው ወንበዴ ግን አልተባበረም ፤ እርሱ ስለእኛ ርጉም ሆነ ፡ ለእኛም ሲል ሐጢአተኛ ተባለ ፡ ብቻውን ቅዱስ የሆነ እርሱ አንዳች እንኳን ሃጢአት ሳይኖርበት ስለእኛ በደለኛ ሆነ ፤ ከሁሉ ይልቅ ብሩክ እርሱ” በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው” ተብሎ ስለተፃፈ ርጉም ተባለ ፤ እንግዲህ ከዚህ በላይ ራስን ባዶ ማድረግ አለን? በፍፁም የለም!! ይህ ነው የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር! ይህ ነው የክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር!

No comments:

Post a Comment