ይህንን ኀይለ ቃል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳሪያ ለሊቀ ሐዋርያት ለቅዱስ
ጴጥሮስ ተናግሮታል፡፡ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወለድ በተለየ አካሉ ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ፡፡ (ዮሐ
1፡14)
ከንጽሕተ ንጹሐን ከድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ ከዘመን አስቀድሞ የነበረ
እርሱ ትንሽ ህፃን ሆኗልና፣ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን በዘላለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ
ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ ኀጢዓትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት ይህን
ወድዷልና፡፡ ክብሩ ተለይቶት የነበረ ሥጋን ክቡር አምላክ ሊያደርገው የጸጋ ገዥነትን አጥቶ የነበረ ሥጋንም የባሕርይ ገዥ ሊያደርገው
ወደደ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ያለውንም ሰው በመሆን ሊገልጠው ወደደ››
(ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 220)