Saturday, January 13, 2018

ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢያተ ዓለም (እነሆ የዓለምን ኃጢያት የሚያስተሰርየው የእግዚአብሔር በግ: ዮሐ ፩፣ ፳፱)





            የጌታ መንገዱን የሚጠርግ መልዕክተኛ እንዳለው አስቀድሞ በነቢየ እግዚአብሔር በኢሳይያስ( ኢሳ ፵ ፣፫- ፭) ላይ የአዋጅ ነጋሪው ዮሐንስ ፴ ዘመን ሲሞላው ለጌታችን መንፈቅ ሲቀረው የንስሐ ስብከትን እየሰበከ የንስሐ ጥምቀትን በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ እያጠመቀ ሲመላለስ ዓለምን ሊቤዥ የመጣውን የቆሮንቶሱን ባህታዊ የዕለተ አርቡን ሙሽራ ዘመኑ ደርሶ ሲመጣ ተመልክቶ እንደሚዜነቱ ለራሱ ደቀመዛሙርት ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢያተ ዓለም ፤የእግዚአብሔር በግ ሙሽራው የዓለምን ኃጢያት የሚያስተሰርየው ፣ትውልደ አዳም ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የጠበቀው መሲህ እርሱ ነው በማለት አስተዋወቃቸው።

ትህትናን ከእናትና ከአባቱ ከካህኑ ዘካርያስና ከቅድስት ኤልሳቤጥ ተምሯልና በስብከቱ እኔስ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ( በ፮ ወር ይቀድመዋልና) ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እራሱም በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋልና መንሹም በእጁ ነው ዐውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራው ይከልታ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ገናንነት ይመሰክር ነበር። (ማቴ ፫ ፣፲፮-፲፯) 

Thursday, January 11, 2018

ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተክርስቲያን አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት




የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን         
==========================

===>ቤተ ኢያኢሮስ የፈውስና የድህነት ቤት ናት ፣አንድም ቤተ ሳህል የምህረት አደባባይ ዘማዊው ድንግል፣ቀማኛው መጽዋች ኀጥኡ ጻድቅ ሆኖ የሚቀየርባት ናት
==>የእግዚአብሔርን ልጅ መድኅን ዓለም ክርስቶስን ለማየት ብቸኛዋ የዘኪዮስ ሾላ፣ አምስት እንጀራና ሁለት አሣ በርክቶ የተመገበባት የጥብርያዶስ ባሕር ማቴ ፲፬፣፲፱
==>የመጀመሪያዋ የዓለማችን መንፈሳዊት የደን ሚኒስቴር አጸዶቿ በገነት አምሳል በተለያዩ ዕፅዋቶች የለመለመች፣
==>ሕመምተኞች በመንፈሳዊ ሐኪሞች ተመርምረው ፈውስና ድህነት የሚያገኙባት መንፈሳዊት ላቦራቶሪ (ማቴ፱፣፴፮)፤
==>በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምኑ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ዳግመኛ የሚወለዱባት (ዮሐ፫፣፭)፤
==>ለሚያምኑት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆኑ ዘንድ አባት ብለው የሚጠሩበትን የልጅነትን ክብር የሚያገኙባት፣ ከሰማዊው ምስጢር ተሳታፊ የሚሆኑባት፤
==>የእግዚአብሔር የፀጋው ግምጃ ቤት በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚታደልባት ፤
የጥበብ ቤት ሰባቱ ምሰሶዎች የተዘረጉባት
በአምስቱ አዕማድ ጸንታ የታነጸች፤
==>የመጀመሪያዋ የትምህርት ሚኒስቴር ፊደል ቀርጻ ብራና ዳምጣ ትውልዱን ያስተማረች፣ የሀገር ኩራት ፊደልን ቀርጻ በቅርስነት ያበረከተች፤
==>የሒሳብ ስሌት ሰርታ የዘመን ሳይንስ ቀምራ አበቅቴና መጥቅን ለይታ የአጿማትና የበዓላትን ዕለታት ወስና የዘመን መቁጠሪያ አዘጋጅታ ለትውልድ ያበረከተች የጥበብ ተቋም፣
==> ምግባራቸውን ያቀኑ ፣ሃይማኖታቸውን ያጸኑ አርአያና ምሳሌ የሚሆኑ፣ ሀገርና ሕዝብ ወዳድ ትውልድን ያፈራች ብቸኛዋ የስነ ዜጋ ትምህርት ቤት
==>እንባ የሚታበስባት ታሪክ የሚቀየርባት ነውር የሚንከባለልባት፣ እንቆቅልሽ የሚፈታባት፣ በትህትና የሆኑ ጻድቃን የሚገቡባት የደብረዘይት ተራራ፤
==>ቅዳሴ የሚቀደስባት፣ ሰዓታትና ማህሌት የሚቆምባት፣የእግዚአብሔር ምስጋና አውድ፤
==>ዘመን የሚሻገር ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍና የሚወረስ ቁሳዊና ራዕያዊ ትውፊትና ቅርስ ያላት
==> ሁሉ ያላት ሁሉ የተረፋት ስንዱ እመቤት ብታውስ እንጅ የማትበደር ፣ ያልተበረዘ ያልተከለሰ ንጹህ ወንጌል የሚሰበክባት፣
==> በነቢያትና በሐዋርያት ላይ የተመሠረተች በማዕዘኑ ራስ ድንጋይ በክርስቶስ የጸናችና የታነጸች፤(ኤፌ፪፣፳)
==>አንድም በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የታነፀች በቅዱሳን ያሸበረቀች በሰማዕታት ደም የከበረች፣
==> ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕሪ አባቱ ከአብ ከባሕሪ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የተካከለ አምላክ መሆኑ የሚሰበክባት፣
==> የእመ አምላክ የወላዲተ ቃል የድንግል ማርያም ክብርና አማላጅነት የሚታመንባትና የሚነገርባት፣
==>የቃል ኪዳኑ ታቦት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለማክበር ና ትውልዱን ለመባረክ በቅድስተ ቅዱሳኗ የሚገኝባት፣ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናት።
-----------------------------------------------------
የካቲት ፳፬ቀን ፳፻፰ዓ.ም.
መምህር.ዲ.ቸርነት ይግረም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጓት ምክንያቶች።



፩- የተመሠረተችው በሰባኪ ወይም በአሳማኝ ወይም በአስገዳጅ ወይም ጥሬ ሃብትና መልክዓ ምድርን በሚሹ ወራሪዎች አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ እንጂ። የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጥምቀት በቀጥታ ከመንፈስ ቅዱስ የታዘዘ ነው። [የሐዋርያት ሥራ ፰፣ ፳]። ጃንደረባው ጥምቀትን እንደጠየቀ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲጀመር ወደ ቅዱስ ማርቆስ መንበር የላኩ አብርሃና አጽብሃ ናቸው።
፪- አይሁድ የነበረች አንዲት አገር በመንግሥት አዋጅ ክርስቲያን የሆነች አገር ኢትዮጵያ ብቻ ስትሆን ይህን ሽግግር የፈጸመች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት።
፫- በአዋጅ፣ በእምቢልታና በእልልታ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥቴ ነው ብላ ያወጀች አገር በምድር ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ስትሆን ይህን አዋጅ በቤተክርስቲያን ቡራኬ ያጸናች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።

ዘመነ አስተርዕዮ: ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ




     ይህንን ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ከወጣ በኋላ እንደ አባትነቱ እንደ እግዚአብሔርነቱ በሰማይ ሆኖ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለት ምስክርነቱን በሰጠበት ወቅት የተናገረው ሲሆን ፤የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ ፣ርግብ እንቁላሏን ቢሰብሩ ከስፍራዋ ካላባረሯት ፣የፊቱን ረስታ እንደገና ሌላ እንቁላል ትጥላለች ለአዲስ ሕይወትም ትዘጋጃለች ፤መንፈስ ቅዱስም እንጅ የዋህና ኅዳጌ በቀል ስለሆነ ምን በደል ቢሰሩ በኃጢያትም ቢወድቁ ፈጽመው ካልካዱት ድረስ እንደማይተው ሲያጠይቅ ፤ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ደረቀ ስትል የወይራ ዝንጣፊ ለምለም ይዛ እንደታየች መንፈስ ቅዱስም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ መወገዱን በደልን ኃጢያት መደምሱን የ፭ሺህ ፭መቶ ዘመን ድርቀት መጥፋቱን የምስራች ይዞ ይገለጣልና ሲል በርግብ አምሳል ተገልጧል።

Wednesday, January 3, 2018

የእረኞች አለቃ ልደት


           ሰው መሆን ያቃታቸውን የሰው ልጆችን ሰው ያደርግ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ
        

 ከምስራቃዊ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም መንደር የብርሃን አምድ ተተከለ በእኩለ ሌሊት ድምጽ ከራማ ከኢዮር ኤረር ሰማያትን ሰንጥቆ ምድርን ያንቀጠቀጠ የዝማሬና የእልልታ ድምጽ ተሰማ በቤተልሔም ከተማ በአለቃና በነገድ ተከፍለው በጨለማ ውስጥ መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞችን የቀሰቀሰ የእረኞች አለቃ ልደት ፤ሌሊቱ ማለፉን ሊያበስር ብርሃን ከብርሃን ወጥቶ በእኩለ ሌሊት ጨለማውን አጠፋው ። አስቀድሞ በነቢያቱ የተናገረውን ይፈጽም ዘንድ በእንስሳት መካከል በበረት ተወለደ "እግዚኦ ሰማዕኩ ድምፀከ ወፈራህኩ ርኢኩ ፤ አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ በሁለት እንስሳት መካከል አየሁህ (ዕንባ ፫፣፪) 

በሬ የገዥውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ እስራኤል ግን አላወቀም ( ኢሳ ፩፣ ፫)