የጌታ መንገዱን የሚጠርግ መልዕክተኛ እንዳለው አስቀድሞ በነቢየ እግዚአብሔር በኢሳይያስ( ኢሳ ፵ ፣፫- ፭) ላይ የአዋጅ ነጋሪው ዮሐንስ ፴ ዘመን ሲሞላው ለጌታችን መንፈቅ ሲቀረው የንስሐ ስብከትን እየሰበከ የንስሐ ጥምቀትን በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ እያጠመቀ ሲመላለስ ዓለምን ሊቤዥ የመጣውን የቆሮንቶሱን ባህታዊ የዕለተ አርቡን ሙሽራ ዘመኑ ደርሶ ሲመጣ ተመልክቶ እንደሚዜነቱ ለራሱ ደቀመዛሙርት ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢያተ ዓለም ፤የእግዚአብሔር በግ ሙሽራው የዓለምን ኃጢያት የሚያስተሰርየው ፣ትውልደ አዳም ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የጠበቀው መሲህ እርሱ ነው በማለት አስተዋወቃቸው።
ትህትናን ከእናትና ከአባቱ ከካህኑ ዘካርያስና ከቅድስት ኤልሳቤጥ ተምሯልና በስብከቱ እኔስ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ( በ፮ ወር ይቀድመዋልና) ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል እራሱም በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋልና መንሹም በእጁ ነው ዐውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራው ይከልታ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ገናንነት ይመሰክር ነበር። (ማቴ ፫ ፣፲፮-፲፯)