Saturday, November 30, 2013

"ስለ ጽዮን ዝም አልልም" (ኢሳ 62:1)




ይህንን የተናገረው ልዑለ ቃል ኢሳይያስ እግዚአብሔር የራቀውን አቅርቦለት የረቀቀውን አጉልቶለት ትንቢት በሚናገርበት ዘመን ሲሆን  ጽዮን የሚለው ስም እንደአገባቡ ይፈታል ልብስ በየፈርጁ እንዲለበስ የቅዱሳት መጽሐፍት ቃልም በስልት በስልቱ ይተረጉማል መጽሓፍ ቅዱስ በትርጉሜ ስልት ሲበለት መልክ መልክ አለው አንዱ ቃል እንደያገባቡ የተለያየ ትርጓሜ ይሰጣል በመሆኑም ከላይ በርዕሳችን የተጠቀሰው የነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ብንመለከት ቃሉ ህብርነት ያለው ሆኖ ይገኛል ጽዮን የሚለው ቃል ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መንግስተ ሰማያት ወይም ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል ኢየሩሳሌም ቤተእስራኤል (ቤተ ያዕቆብ) ቤተ መቅደስ ተብሎ የሚፈታበት ጊዜ አለ በሌላ ሥፍራ ደግሞ የቃሉ አገባብ ኢየሩሳሌም ድንግል ማርያም ወይም መስቀል ክርስቶስ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል እንግዲህ አርዕስትን ተመልክቶ ስለምን እንደተነገረ በማስተዋል ካላዩት ካልመረመሩት በዘፈቀደ እንተርጉም ቢሉት ምስጢሩ ሊገኝ አይችልም ትርጓሜውም የተሳሳተ ይሆናል ከምሥጢር ዳህፅ(መሰናክል) ለመጠብቅ መጻሕፍት መመርመር መምህራንን ማነጋገር በጸሎት በትህትና እግዚአብሔርን ግለጽልን በማለት: ይህን ቃል የተለያየ ትርጉም እንዳለው ለማሳየት በምሳሌ እንመልከት:-

Thursday, November 21, 2013

ክፍል ሦስት ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



ክፍል ሦስት
‹‹የእግዚአብሔር ቃል›


ካለፈዉ የቀጠለ….
የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው ስንል ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር በመለኮት፤ በአገዛዝ በሥልጣን በሕልውና የተስተካከለ ነው::
ከላይ ባየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መረጃዎች መሠረት ፈጣሪነት የእግዚአብሔር ብቻ ነውና፤ ቃል የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን እንገነዘባለን መናፍቃን ይህን እውነት ላለመቀበል (ቆላ 9፡15፣ 1ኛ ጢሞ 3፡6፣ 2ኛ ቆሮ 4፡4፣ ዕብ 1፡3) ያለውን ንባብ ‹‹የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ ክርስቶስ›› ፤ ‹‹እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው›› ፤ ባሕርይ ምሳሌ ሆኖ ያለውን እና በሐዋ 17፡31 በዚያን ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጻድቅ ሊፈርድ አለው የሚለውን ጥቅስ በመጥቀስ ክርስቶስ ምሣሌ እንጂ አማናዊ እግዚአብሔር አይደለም ሐዋርያው እግዚአብሔር ነው አላለም፤ እንዲሁም በዕብ 1፡2 ‹‹ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ›› የሚለውን ጥቅስ ፈጥሮ ፈጠረበት ለማለት ነው ‹‹ባዘጋጀው ሰው እጅ›› የሚለውም ይህንኑ ሐሳባችን ይደግፋል ይላሉ ሎቱ ስብሐት ይህ አመለካከታቸው ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነታ ውጪ ፍጹም ክህደት ነው፡፡
1.   በመጀመሪያ ምሣሌ የሚለውን ቃል አጠቃቀም በፊልጵ 2፡6-8 ባለው ጥቅስ ውስጥ ጠቅለል ባለ ሁኔታ ስለሚገኝ ከወልድ ማንነት ጋር እያገናዘብን እንመልከት
‹‹እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቃማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረም ነገር ግን የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሣሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ በምስሉም እንደሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳን የታዘዘ ሆነ ይላል›› ፊልጵ 2፡6-8
ክርስቶስ ከኃጢዓት በቀር ሰው ሆኖ በዚች መሬት ላይ ሲመላለስ ሲያስተምር፤ ተአምራት ሲሰራ፣ ሲታይ፣ ሲዳሰስ ፣ ሲጨበጥ ፣ እንደነበር ምንም የማያጠራጥር እውነት ሆኖ ሳለ (በዮሐ 1፡14፤ ዕብ 2፡17፤ ዕብ 4፡15፤ ፊልጵ 2፡6)
በሰውም ምሣሌ በሰውም መልክ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎ እናገኛለን ታዲያ ሰው መሆኑን እያወቅን በሰው ምሣሌ በሰው መልክ በማለት ብቻ ሰው አይደለም አልሆነም ማለት ይገባልን? ማለትስ እንችላለን? እናስተውል በደመ ነፍስ በሥጋ ኅሊና የምንቀሳቀስ እስከመቼ? ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው ያለመለወጥ ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመጠፋፋት፣ ያለመደባለቅ፣ ያለመዋዋጥ የቃልን በተዋህዶ ሰው መሆን ነው በተመሳሳይ ሁኔታ በእግዚአብሔር መልክ፣ በእግዚአብሔር ምሳሌ ሲልም እንደዚያው ሰው ሲሆን በሰው መልክ፣ ሰው ሲሆን በሰው ምሣሌ እንዳለው ነው፡፡
2.   ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑ ሲታወቅ ሳለ በሰው ምሣሌ፤ በሰው መልክ፤ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በእግዚአብሔር ምሣሌ፣ በእግዚአብሔር መልክ ማለት ምን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው? ምንስ ለመግለጽ ነው? ብሎ የሚጠይቅ ቢኖር እንደሚከተለው ይሆናል መልሱ፡-
ቅድመ ተዋህዶ ቃልና ሥጋ እየራሳቸው ነበሩ በዚህም ምክንያት ቃል በፈጣሪነቱ ልዑለ እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራ ነበር፤ (ዮሐ 1፡1) እንዲሁም ሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተገኘ በመሆኑ በቅድስት ድንግል ማርያም ሰው መሆን ሰው ተብሎ በተገዥነት፤ በፍጡርነት ይመለ ክ ነበር ቃል ትንቢቱ የሚፈፀምበት ዘመን ሲደርስ በክብር ሳለ የሰውን ልጅ ድህነት ለመፈፀም በፈቃዱ ዝቅ ብሎ ከሥጋ ሲዋሐድ ሥጋ ከዝቅተኛነት እጅግ ከፍ ብሎ እንዲዋሐድ አድርጓል፡፡
ቃልና ሥጋም በፍጹም ተዋህዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኑ (ዮሐ 1፡14) በተዋህዶ አንድ የመሆናቸውም ሥም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ አማኑኤል ተባለ (ማቴ 1፡21-23) የተዋህዶ ስም ያስፈለገውም ከተዋህዶ በኋላ ምንታዌ (ሁለትነት) ስለሌለ ነው፡፡
‹‹ቃል›› በተለየ አካሉ በተለየ ግብሩ በፍጹም እግዚአብሔርነት ላይ ያለመጠፋፋት፣ ያለመደባለቅ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመለወጥ በተዋህዶ ፍጹም ሰው በመሆኑ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት በሚናገርበት ጊዜ መለኮት ወደ መሆን አለመለወጡን፣ የሥጋ አምላክነት በውላጤ ሳይሆን በተዋህዶ መሆኑን ለመግለጽ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በእግዚአብሔር ምሳሌ ብሎታል (ቆላ 2፡9) ይህም እግዚአብሔር ብቻ መባል የቅድመ ተዋህዶ ስም ነበረና ምስጢር ሲያስጠብቅና ሲያስተምር ነው፤ እንጂ ኢየሱስ እግዚአብሔር አይደለም ለማለት አልፃፈም፡፡ እንዲሁም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ሲገልጽ ደግሞ መለኮትና ስጋ አለመጠፋፋታቸውን፤ የመለኮትን በሥጋ አለመዋጥ አለመለወጥና በፍጹም ውህደት ለማስተማር ሰው መሆኑን በተለያየ ቦታ ጽፎ ሳለ፤ በሰው መልክ በሰው ምሣሌ ሆኖ ይላል፤ የሥጋን በተዋህዶ አምላክ መሆን መግለጽ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ምስጢረ ተዋህዶን ያስተማረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን በእግዚአብሔር ምሳሌ በማለት ፈንታ እግዚአብሔር ብቻ ቢል ሥጋ መለኮት ወደ መሆን ተለወጠ ወይም ቃል ቅድመ ተዋህዶ ሥጋ ነበረው ስለሚያሰኝ ትምህርቱ የተዋህዶ መሆኑ ቀርቶ የውላጤና የህድረት በሆነ ነበር፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ በሚናገርበት አንቀጽ ሁሉ ተዋሕዶን በከፍተኛ ጥንቃቄ ሳይገልጽ ያለፈበት ቦታ የለም በዕብራውያን መልዕክቱም ለዕብራውያን ሰዎች ታላቅነት ባለው ዙፋን በአብ ቀኝ መቀመጡንና ከመላዕክት መብለጡን ከጻፈላቸው በኋላ ሰውነቱ ተለውጦ ቢጠፋ ወይም ጥንቱንም ሰው ባይሆን ይሆናል እንዳይሉ የቀደሳቸው እርሱና የተቀደሱት እነዚያ ከአንድ ከአዳም ስለተወለዱ ሁሉም አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህ ወንድሞቼ ይል ዘንድ አያፍርም በማለት ይገልጻል፤ እንደዚህም ማለቱ ልጆች (ሐዋርያት) በሥጋና በደም እንደተገናኙ እርሱም በሞቱ ዲያብሎስን ድል አድርጎ ሞትን በመፍራት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ነጻ ያወጣ ዘንድ በዚሁ በሥጋና በደም ተገናኝቶአቸዋል ሲል ነው (ዕብ 1፡4 እና ዕብ 2፡14)
ይህንኑም ከልጆቹ ጋር የተገናኘበትን ሥጋና ደም (አካል) ከአብርሃም ዘር ነሣ እንጂ ከመላዕክት አካል ያነሣ አይደለም፤ የሚያስታርቃቸው የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው ይላል (ዕብ 2፡15-18) ይህንንም ሊሆን የተገባው የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህን ሥራው የበግ መስዋት ሰውቶ ለራሱና ለሕዝቡ የኃጢዓት ሥርየት ከእግዚአብሔር መለመን ብቻ ስለነበረ የአዲስ ኪዳን ሊቀካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን መስዋዕት አድርጎ አቅርቦ ከአባቱ ጋር ከማስታረቅ ሌላ ራሱም ከአባቱ ጋር ሆኖ ታራቂ ይቅር ባይ ስለሆነ ነው (ቆላ 3፡13) በመሆኑም የኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን የመምሰል ታላቁ ምስጢር ያለ ጥርጥርም ይሄው ነው (1ጢሞ 3፡16) ብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ ጥሩ ምንጭ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 254-255 ላይ እንደተረጎሙት ‹‹የክብሩ ብርሃንና የባሕርይ ምሣሌ (ዕብ 1፡2-3) ማለቱ አባታቸውን በመልክ የማይመስሉ ብዙ ልጆች ይገኛሉ ነገር ግን የልጅ መልኩ ምንም እንኳን ወደ ቀኝ ወደ ግራ ወደላይም ያሉትን ትውልድ ቢመስል በጣም ደስ የሚያሰኝ ልጅ አባቱን ሲመስል ነውና ቅዱስ ጳውሎስ የመልኩ ምሳሌ ማለቱ ክርስቶስ በእውነት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መሆኑን ለማስረዳት ሰለ አሰበ ነው በማለት በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ እንዲሁም (ዕብ 1-2) በሚመለከት ቅዱስ አትናቴዎስና ብላቴን ኅሩይ ወልደስላሴ እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡
‹‹የእግዚአብሔር ቃል እኛን ለመፍጠር የተፈጠረ አይደለም እኛ በእርሱ ተፈጠርን እንጂ በእርሱ ሁሉ ተፈጠረ ለእኛ ለድኩማን መፈጠሪያ እንዲሆን ልዑሉና ኃያሉ እንደ አገልግሎት መሣሪያ ተፈጠረ ብሎ ማውራት ከደካማ አስተሳሰብ የተገኘ ነው››
ዓለምን እንደፈጠረ አያጠራጥርም ‹‹ቃል›› ምን ጊዜም ነበረና፤ ምን ጊዜም ባሕርያዊ ነው፤ በእርግጥ ያለ ቃል ምንም አልተፈጠረም ያለ እጅ ምንም መስራት እንደማይቻል ‹‹እጁ (እዱ) ይባላልና (መዝ 143፡7) አብ በወልድ ዓለምን ፈጠረ በእጅ ጥልፍ እንደመጥለፍ ሥዕል እንደመሳል ነው ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ የሚለውን ሲተረጉም ቃሉን ሰምቶ ትዕዛዙን ሊፈጽም የሚሮጥ ተወራጅ አሽከር ነበር ማለት አይደለም ይህ በሰዎች ዘንድ በሰዎች ባሕርይ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ራሱ ፈጣሪ ነው፤ የአብ ፈቃድ እርሱ ራሱ ነው….››
እግዚአብሔር ራሱ ዓለምን ፈጠረ እንጂ ሌላ የሚፈጥርለት አላስፈለገውም እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠር እስካለመቻል ደርሶ ደካማ ወይም ዓለምን ለመፍጠር እስካለ መፍቀድ ደርሶ ትዕቢተኛ አይደለም፤ (በማቴ 6፡25 ፣ 10፡29) ያለውን ጠቅሶ እግዚአብሔር በቀጥታ ለፍጥረቱ እንደሚያስብና ካለመኖርም ወደ መኖር እንዳመጣው ያስተምራሉ (የቤተክርስቲያን ታሪክ በአለም መድረክ ገጽ 95)
ብላቴን ኅሩይ ወልደስላሴም ‹‹ዓለሙን ሁሉ በእርሱ በፈጠረበት ማለቱ ልጅ የሚወርሰው ሳይወለድም ከተወለደም በኋላ በአባቱ እጅ የተገኘውን ነው እንጂ ራሱ ሰርቶ ያገኘውን ወረሰ አይባልም ክርስቶስ የወረሰው ግን በእርሱ የተፈጠረውንና እርሱም የፈጠረውን ሁሉ ነው ከአባቱ ብቻ የተሰጠውን አይደለምና ከወራሽም ልክ የበለጠ ክብር እንዳለው ለዕብራውያን ለማስረዳት ነው ይላሉ፡፡››
በ(ሐዋ 17፡31) ‹‹ባዘጋጀው ሰው›› የተባለው ያለመለወጥ ያለ መቀላቀል ‹‹ቃል›› ሰው ሆኖ የሰው ልጅ ሊሞተው የሚገባውን ሞት ሞቶ ሕይወትን ሰጥቶአል እንዲሁም ቃል በሰውነት አንድ ጊዜ ለዘላለሙ ለፍርድ ቀን ወደዚህች ምድር ይመጣል በዚያን ጊዜም አብ በወልድ ሕልው ሆኖ ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ይፈርዳል ማለት ነው፡፡ (ዮሐ 5፡22-29 ፣ ዮሐ 12፡48 ፣ ራዕ 1፡7) ‹‹አዘጋጀ›› የሚለውን ቃል ስንመለከት ደግሞ ፈጠረ ከሚለው ቃል የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ ለምሣሌ፡
ሰው ራሱን ለተለያየ ነገር ያዘጋጃል፤ ክርስቲያኖችም በመጽሐፍ ቅዱስ ለመንግስቱ እንዲዘጋጁ ታዘዋል እንዲዘጋጁ ማለት ግን ራሳቸውን ለመንግስቱ እንዲፈጥሩ ማለት አይደለም ወይም ራሱን የሚያዘጋጅ ራሱን ይፈጥራል ማለት አይደለም መፍጠር ካመኖር ወደ መኖር መምጣት ነው ነገር ግን አዘጋጀና ፈጠረን አንድ አድርገው የሚመለከቱ ወንድሞች አሉ እነርሱን የሚደግፍ የሚመስላቸውን ጥቅስ ሁሉ ይጠቅሳሉ ከነዚህም አንድ (ዮሐ ራዕ 3፡14) ነው ‹‹የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የነበረው እንዲህ ይላል››
ጥቅሱ፡- ወልድን አልፋ ኦሜጋ መጀመሪያና መጨረሻ መሆኑን ይናገራል እንጂ በመጀመሪያ ቀን የተፈጠረው ነው አይልም መጀመሪያ የተፈጠሩ ሰማይና ምድር መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ (ዘፍ 1፡1) ይናገራል እንዲሁም ፍጥረታት ሁሉ የተፈጠሩት በቀንና በዘመን ነው ቀንና ዘመን የማይቆጠርለት እግዚአብሔር ብቻ ነው ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ እግዚአብሔር ስለሆነ ዘመን አይቆጠርለትም ዘመናትን የፈጠረ የዘላለም ጌታ ነው፡፡ (ዕብ 1፡2-22 ፣ መዝ 101፡25-27 ፣ ሚክ 5፡2 ፣ ኢሳ 9፡6)
ይህ ሲባል ግን የተዋሐደው ሥጋ በቅድምና በሰማይ ነበረ ማለት አይደለም ሥጋ ቀዳማዊ የሆነው በተዋህዶ ነው፤ የማይሞተው በተዋሐደው ሥጋ ሞተ እንደተባለ ሁሉ (ሐዋ 2፡2) (1ኛ ጴጥ 3፡18)         
1.  ከአብ ጋር በመስተካከል
የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው ስንል ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር በመለኮት፤ በአገዛዝ በሥልጣን በሕልውና የተስተካከለ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይም ሆነ በሐዲስ እውነተኝነቱ የተመሰከረለት ከእግዚአብሔር የሚስተካከል የለም፤ እንዲያውም ከእርሱ ጋር የሚስተካል ፍጡር ዋጋው ሞት የሚወልድ ኀጢዓት ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር በመሆኑ ራሱን ከባሕርይ አባቱ ከአብ አስተካከለ ምክንያቱም የባሕርይ አባቱ አብ እግዚአብሔር ስለሆነ የባሕርይ ልጁም ወልድ እግዚአብሔር ነውና (ማቴ 16፡16)
1.   ‹‹ኢየሱስ ግን አባቴ እስከዛሬ ይሠራል እኔ ደግሞ እሠራለሁ ብሎ፤ መለሰላቸው ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ሳለ አለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር (ዮሐ 5፡17 ፣ ዮሐ 18 ፣ ዮሐ 21 ፣ ዮሐ 23)››
2.   ‹‹እኔና አብ አንድ ነን እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ ባደርገው ግን እኔንስ እንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እደሆነ እኔም በአብ እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ›› (ዮሐ 10፡30-38)
3.   ‹‹በእኔ የሚያምን ሁሉ በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም ፤ እኔን የሚያይ የላከኝን ያያል›› (ዮሐ 12፡44-45)
4.   እኔን ያየ አብን አይቷል…. እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ (ዮሐ 14፡9-11)
5.   እራሱ ያከብረኛል ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ (ዮሐ 16፡14-15)
6.   ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው (1ኛ ዮሐ 2፡23)
7.   ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረም›› (ፊልጵ 2፡6)
እነዚህ ጥቅሶች የሚያስተምሩት የወልድን ከአብ ጋር መስተካከልና በሕልውና አንድ መሆናቸውን ነው፤ ይህን በሚመለከት ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ ያስተምረናል ‹‹ቅዱስ ጳውሎስ የክብሩ መንጸባረቅ ያለውን ይዞ አትናቴዎስም አብና የወልድን ሕላዌ በፀሐይ ፤ በፀዳሉ መስሎ ይናገረዋል፤ የፀሐይ መኖር በጸዳሉ የእሳት በነበልባሉ እንዲታወቅ አብን ያወቅነው በወልድ ነው ጸዳል ከብርሀኑ እንደማይለይ ወልድ ከአብ አብም ከወልድ አይለይም ፀሐይና ጸዳል ሁለት ፀሐዮች እንደማይባሉ አብና ወልድም ሁለት አማልክት አይባም ይላል፡፡
አንዳንድ መናፍቃን ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› የሚለውን ላለመቀበል ‹‹አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምንሃለሁ:: እኛም አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ እኔም በእርሱ አንተም በእኔ ስትሆን በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ የሠጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ›› (ዮሐ 17፡21-22) የሚለውን እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡
በመሠረቱ ሐዋርያት በአካል የተለያዩ የመሆናቸውን ያህል በክርስቶስ አንድ ናቸው ይሁንና የጥቅሱ ምስጢር እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን ገባ ብሎ ማየት የሚጠይቅ ነው፡፡ ሐረግ በሐረግ ማየትና ማብራራትን ይሻል፡-
‹‹በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ›› ሲል እኔ በአንተ ሕልውና እንዳለሁ አንተም በእኔ ሕልውና እንዳለህ በሕልውና አንድ አምላክ እንደሆንን በእኛ አንድነት በማመን አንድ እንዲሆኑ እለምናለሁ ማለት ነው፡፡ ፍቃዱ እንደሆነ ፍቃድህ ይሁን ማለትና በአንጻሩም ራስን ዝቅ የማድረግ ትምህርቱን ‹‹እለምንሀለሁ›› በማለት ያስተምራል ዮሐ 13፡1-20 ፣ ማቴ 11፡28-30 ፣ 2ኛ ቆሮ 8-9 ፣ ፊልጵ 2፡1-8
‹‹እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ›› ማለቱ ወልድ መካከለኛ ሰውና አምላክ በመሆኑ በመለኮቱ ከአብ ጋር በሰውነቱ ከአዳም ልጆች ጋር አንድ መሆኑን መግለፅ እንጂ ከአብ ጋር ያለውን አንድነት እንደሌለ ለማድረግ የተጻፈ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የኑሲሱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ‹‹ክርስቶስ ማለት ፈጣሪና ፍጡር በአንድ አካልና በአንድ ባሕርይ አንድ የሆነ ማለት ነው›› ብሏል፡፡ (ሃይ.አበው.ገጽ 119)
2.  በስም
የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው ስንል ማንኛውም ፍጡር ሊጠራበት የማይችለውን የፈጣሪን ባሕርያዊ ስም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ልጁ በመሆኑ ባሕርያዊ በሆነው ‹‹እግዚአብሔር›› በሚለው ስም ተጠርቷል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር የሚባል ‹‹እግዚአብሔር›› ነውና መድኃኒታችንን ኢየሱስን እግዚአብሔር እንለዋለን ለዚህም ነቢያትና ሐዋርያት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
1.   ‹‹እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ›› መዝ 46፡5
የዐረገውና እግዚአብሔር የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው አብ ሥጋን አልተዋሐደምና ዐረገ አይባልም፡፡ (ሐዋ 1፡9-10 ፣ ማር 16፡19)
2.   የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል ይመጣልና በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና (መዝ 95፡13)
·         ለፍርድ የሚመጣው ክርስቶስ በመሆኑ፤ ለፍርድ ይመጣል የተባለው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ማቴ 12፡36 ፣ ዮሐ 5፡23-27)
3.   በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ ባሕርና ሞላዋ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ ተራሮች ደስ ይበላቸው በምድር ሊፈርዱ ይመጣልና (መዝ 97፡9)
4.   የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሳልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፈራል (ኢሳ 24-23)
5.   እነሆ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃይል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው (ኢሳ 40፡10 ፤ ራዕ 22፡12)
6.   የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ተጽፏል (ዮሐ 20፡31)
7.   እነሆ ለዳዊት ቁጥቋጦ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል የሚጠራበትም ስም እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው (ኤር 23፡5) እግዚአብሔር ጽድቃችን ማለት እውነተኛን የባሕርይ አምላክ እውነተኛ እግዚአብሔራችን ማለት ነው፡፡ ይህም ‹‹ክርስቶስ እኔ እውነት ሕይወትም ነኝ›› ካለው ጋር ይስማማል (ዮሐ 14፡6)
8.   በአምላካቸው በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በሰልፍ ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም አለው (ሆሴ 1፡6-7) በአምላካቸው አድናቸዋለሁ ያለው እግዚአብሔር ሲሆን አዳኙም እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ አዳኝ የተባለ እግዚአብሔር በተለየ አካሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
9.   በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ (ዮሐ 1፡1)
10.  ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ሐዋ 20፡28
11. በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረም (ፊልጵ 2፡6)
12. እኔ ፊተኛ ነኝ እኔ ኋለኛ ነኝ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም (ዘፀ 3፡13 ፣ ኢሳ 44፡6 ፣ ኢሳ 41፡4 ፣ ኢሳ 48፡12)
‹‹ፊተኛው መጨረሻው ሕያውም ነኝ ሞቼ ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ›› (ራዕ 1፡8 ፣ ራዕ 2፡8 ፣ ራዕ 1፡18 ፣ ራዕ 22፡13)
በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነቢያት በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመሳሳይ ምስክርነት መስጠታቸው ሁለቱንም ያናገረ የእውነት መንፈስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከመሆኑም ባሻገር ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለመሆኑ ግልጽና በቂ ማስረጃ ነው፡፡
3.  በመድኃኒትነት
‹‹እግዚአብሔር መድኃኒቴ ነው›› ፤ ‹‹ቁሙ የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ›› (መዝ 26፡1 ፣ ዘጸ 14፡14) ብለው እንደመሰከሩ ነቢያቱ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነውና አዳኝ መድኃኒት ነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ መድኃኒት ነው ይህም በባሕርይ እግዚአብሔር መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ይገልጽልናል፡፡ ምክንያቱም በመድኃኒትነቱ ሕዝበ እስራኤልን የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና ሌላም አዳኝ እንደሌለ መጽሐፍ ቅዱስ በ(ኢሳ 45፡21 ፣ ኢሳ 43፡3 ፣ ኤር 14፡8 ፣ ሆሴ 13፡4) ላይ ይገልጻል የክርስቶስን አዳኝነት ደግሞ በሙሉ አዲስ ኪዳን ይገልጻል ከዚህ መካከል የሚከተሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡
1.   ‹‹ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኀጢያታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ›› (ማቴ 1፡21)
2.   ‹‹አሁን የምናምን ስለቃልሽ አይደለም እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር›› (ዮሐ 4፡42)
3.   ‹‹እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው መዳንም በሌላ በምንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና›› (ሐዋ 4፡11-12)
4.   ‹‹አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕጻን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ›› (ሉቃ 2፡11-12)
5.   በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘለዓለም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን አሜን (ይሁዳ 1፡25)
4.  በታራቂነት
መሐሪነት ይቅርባይነት ታራቂነት የእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫ ነው በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ከበደላችን ከኃጢዓታችን ሁሉ ይቅር ብሎናል የዕዳ በደላችንንም አጥፍቶ መርገማችንን ሽሮልናል፡፡
አዳም መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዳይበላ ያዘዘው እግዚአብሔር ነው ትዕዛዙንም በማፍረሱ ከገነት ያስወጣው እግዚአብሔር ነው ስለዚህ አዳም በንስሐ ይቅር በለኝ ብሎ መታረቅ ያለበት በደሉ ካረፈበት ከእግዚአብሔር ነው ይቅር ማለት መታረቅም የተበዳዩ የእግዚአብሔር ነው ይህ ሲሆን ሳለ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቦታ ይቅር ባይ ታራቂም በመሆኑ እግዚአብሔርነቱ ቅንጣት ያህል አያጠራጥርም ምክንያቱም ሳይበድል ይቅር አይልም ካልተጣላውም አይታረቅም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ (የእግዚአብሔር ቃል) ከራሱ ጋራ አስታረቀን ይቅር አለን ይላል ይህም የሆነው ‹‹ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ (ራሱ መስዋዕት አቅራቢ) ፣ በእርሱም ሁሉ ለሆነ (ራሱ የኃጢዓት መስዋዕት)፣ ለእርሱ ተገብቶታልና ራሱ መስዋዕት ተቀባይና ታራቂ ይቅር ባይ በማለት ግልጽ አድርጎ ጽፎታል›› (ዕብ 2፡10) ፤ ‹‹የሆነው ሁሉ በክርስቶስ በለበሰው ሥጋ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ (ይታረቅ) ነበረና›› (2ቆሮ 5፡18) ‹‹እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ በእርሱ እንዲኖር በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ከራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና›› (ቆላ 1፡19-20) ‹‹ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ምህረት እንዳደረገላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ›› (ቆላ 3፡13)
5.  በምሉዕነት
እግዚአብሔር ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የሌለው አልፋ ኦሜጋ በቦታና በመጠን የማይወሰን በምልዓትና በርቀት ያለ ኃያልና ልዑል አምላክ ነው በሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ እግዚአብሔር ‹‹ምሉዕ በኩለሄ›› መሆኑ ተገልጽዋል፡፡ (በኤር 23፡24 ፤ 1ኛ ነገ 8፡27 ፤ መዝ 138፡7) ‹‹ሰው በስውር ቢሸሸግ እኔ አላየውምን ሰማይና ምድርን የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ›› ይላል፡፡ ዓለም ልትወስነው የማይቻላት በሁሉ ምሉዕ የሚሆን እግዚአብሔር ብቻ ነው ፍጡር ምንም ቢተልቅ ፣ ምንም ቢገዝፍ ፣ ምንም ቢረቅ ውሱን እንጂ ምሉዕ አይባልም፡፡
ጌታችን መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እግዚአብሔር በመሆኑ በዓለም ሁሉ ምሉዕ ስለሆነ ስለ ምሉዕነቱ ሐዋርያት አስተምረውናል
1.   ‹‹እርሷም አካሉና ሁሉን የሚሞላ የእርሱ ሙላት ናት›› (ኤፌ 1፡23) ‹‹ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማይ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው›› (ኤፌ 4፡7-13) ‹‹ነገረ ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው›› (ቆላ 3፡11 ና 20 ፤ ዮሐ 1፡10)
በሁሉ መሙላትና በሁሉ መሆን ለፍጡር አይቻለውም የእግዚአብሔር የግል ሀብቱ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉ የሚቻለው የእግዚአብሔር ‹‹ቃል›› እግዚአብሔር በመሆኑ ‹‹ሁሉ ነው በሁሉ ነው››
‹‹ይቆየን››

Wednesday, November 20, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን





ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፤
 (ክፍል ፩)

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው)፤. . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።
በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።

Friday, November 15, 2013

አቤቱ የሆነብንን አስብ





አቤቱ የሆነብንን አስብ
ይህን የሰቆቃና የተማጽኖ ልመና ወደ እግዚአብሔር ያቀረበ ታላቁ ነቢይ ኤርሚያስ ሲሆን ኤርሚያስ ማለት የቃሉ ትርጉም እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል እግዚአብሔር ያነሳል ማለት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከወደቅንበት አዘቅት ከተጣልንበት መከራ ያንሳን ከፍ ከፍ ያድርገን፡፡
ዘመኑ ክብር ከእስራኤል የለቀቀበት የይሁዳ (የእስራኤል) ክፋት የባሰበት ፍርድ የተጓደለበት ደሀ የተበደለበት አምልኮ ጣዖትና ክህደት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የተስፋፋበት ክፉ ዘመን ነበር፤ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያ ዘመን ከዛሬው ከኢትዮጵያውያን ዘመን ጋራ የሚመሳሰልበትን አመስጥረው ያስተምራሉ፡፡
ዛሬም ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ክብር ጓድሏል መተማመን ጠፍቷል ወንድም በወንድሙ ላይ እተነሣ ፍቅር በመካከላችን ቅዝቅዟል ፍርድ ተጓድሏል ደሀ ተበድሏል በገዛ ሀገራችን ሳይቀር እንደ መጻተኛ የሰሜኑ፣ በደቡብ፣ የምስራቁ ከምዕራብ ተዘዋውሮ እንዳይሰራ ጎጆ ቀልሶ ኑሮ መሥርቶ ወልዶና ከብዶ እንዳይኖር በዘረኝነት አጥር ተከልሎ በገዛ ሀገሩ ስደተኛ በባዕድም ሀገር በአሕዛብም ምድር ሳይቀር ከርታታና ተስፋ ቢስ ሆነናልና፡፡



Wednesday, November 13, 2013

ክፍል ሁለት ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



ክፍል ሁለት
 ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›
                           






                                                      2/ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው
እግዚአብሔር የሚለው ስም የተወደደ ፣ የተቀባ ወይም የግብር ስም ያይደለ የባህርይ ስም ነው፡፡ እግዚአብሔር በየቋንቋው የተለያዩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስሞች አሉት፤ ነገር ግን ሁሉም ባሕርያዊ ስለሆኑ እና እግዚአብሔርም በባሕሪው አንድ ስለሆነ በአንድነት ፈጥሮ በሚገዛበት በባሕሪይ የግብር ስሙ በመጥራት ይተባበራሉ ወይም አንድ ይሆናሉ በየአንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ትርጉም ብንመረምር የምናገኘው እያንዳንዳቸው እግዚአብሔርን የሚጠሩት በኃያልነት፣ በፈጣሪነት፣ በዘላለማዊነት፣ በቸርነትና ሁሉን አድራጊነት መሆኑ ነው ስለዚህ ይህን መሆን የሚቻለው ፍጡር ባለመኖር ለእግዚአብሔር ብቸኛ የባሕሪ ስሙ ሲሆን ለፍጡር ሊሰጡት የማይገባ ቢሰጡትም የማይስማማው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በየቋንቋው ያለ የእግዚአብሔር ስሞች ባሕሪውን ይገልጣሉ፤ እንደ ስሞቹ እንደሚሰራም ያረጋግጣሉ፡፡ (ዘፀ 15፡3 ፣ አሞ 4፡13)
እግዚአብሔር የሚለው ስም የአብ የወልድ የመንፍስ ቅዱስ የወል መጠሪያ ስም ነው የአንፆኪያው ሊቀጳጳስ ቅዱስ ባስሊዮስ ‹‹እኔስ እግዚአብሔር ባልኩ ጊዜ ስለ አብ ስለወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ ነው›› እንዲል እግዚአብሔር የሥላሴ የአንድነትም የሦስትነትም መገለጫ ነው ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር›› ዘፍ 1፡26 ቅዱስ አትናቲዎስም ‹‹አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ስንል እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለታችን ነው›› በማለት ነው ያስተማረው፡፡




Friday, November 8, 2013

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ




የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ
ባለፈው ጽሑፋችን አማላጅነት ከመቼ ጀምሮ እንደነበረ የአማላጅነት ትርጉም ቅዱሳን በአፀደ ስጋ እንደሚያማልዱ እግዚአብሔር የወዳጆቹን ጸሎት እንደሚስማና የለመኑትን ሁሉ እንደሚፈጽሙላቸው አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ማማለድ ይችላሉን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ያስችለን ዘንድ አስቀድመን የሰውን ተፈጥሮና ከሞት በኋላ የሚገጥመውን ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመግቢያት እናያለን፡፡
የሰው ልጅ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው (ዘፍ 1፡26) ሰው ሥጋው ከምድር አፈር የተሠራ ቢሆንም ሥጋ ብቻ አይደለም ከሥጋ ጋር የተዋሃደች ነፍስ ደግሞ አለችው ፡፡ ስለዚህ ሰው በሥጋው የሚራብ የሚጠማ የሚበላ የሚጠጣ የሚደክም የሚታመም የሚዋለድና የሚሞት ሲሆን በነፍሱ ደግሞ የማይሞት የማይራብ የማይፈርስ የማይበሰብስ አሳቢ አዋቂ ተናጋሪ ሕያው ነው፡፡ ሰው ሲሞት ሥጋው ወደ ተፈጠረበት አፈርነቱ ይመለሳል ይፈርሳል ይበሰብሳል ነፍሱ ግን ሕያው ስለሆነች እንደ ስራዋ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሥጋቸው በምድር እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ሥፍራ ሲቀበር ነፍሳቸው ደግሞ በገነት ውስጥ እንደመላእክት በደስታ ይኖራሉ፡፡



‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



‹‹የእግዚአብር ቃል›
በዚህ ርእስ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ስንል ከሶስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍፃሜ የሌለውና የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ስለሆነው ስለ ጌታችን ስለ መድሃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለባሕርይ ህይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል ለሆነውንና በቅድምና በልዕልና ስለነበረው የዘመኑ ፍፃሜ በሆነ ጊዜ የተቆጠረው ሱባኤ ሲያበቃ የተነገረው ትንቢት ሲደርስ ፀጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ ስላደረው አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ወልድ ማንነት ለመፃፍ ፈልገን ነው፡፡
ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሀንስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሄር ነበረ፣ ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡››(ዮሐ 1፣1-2) ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ ፀጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን››(ዮሐ 1፣14)በማለት አስተምሮናል፡፡